መዝሙር 141 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየማታ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ እጣራለሁ፤ በፍጥነትም እርዳኝ! ወደ አንተም ስጮኽ ስማኝ! 2 ጸሎቴን እንደ ዕጣን፥ የተዘረጉትን እጆቼን እንደ ማታ መሥዋዕት አድርገህ ተቀበል። 3 እግዚአብሔር ሆይ! ለአፌ ጠባቂ አኑር፤ በከንፈሮቼም በር ላይ ዘበኛ አቁም። 4 ስሕተት ለማድረግ ከመመኘትና ከክፉ አድራጊዎች ጋር በክፉ ሥራ ከመተባበር ጠብቀኝ፤ የበዓላቸው ግብዣ ተካፋይ ከመሆን ጠብቀኝ። 5 ደግ ሰው በቅንነት መንፈስ ሊቀጣኝና ሊገሥጸኝ ይችላል፤ ከክፉ ሰዎች ግን ክብርን እንኳ አልቀበልም፤ ዘወትርም ክፉ ሥራቸውን በመቃወም እጸልያለሁ። 6 ዳኞቻቸው በገደል አለት ላይ በተጣሉ ጊዜ ሕዝቦቻቸው የእኔ ቃል እውነት መሆኑን ያረጋግጣሉ። 7 መሬት እንደሚታረስና ጓሉ እንደሚፈራርስ የእነርሱም አጥንቶች በመቃብር አፍ ላይ ይበታተናሉ። 8 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እኔ ግን በአንተ መተማመኔን አልተውም፤ የአንተንም ጥበቃ ስለምፈልግ እንድሞት አታድርገኝ! 9 ከዘረጉብኝ ወጥመድ ጠብቀኝ፤ ከክፉ አድራጊዎችም መሰናክል አድነኝ። 10 እኔ ያለ ጒዳት ሳልፍ ክፉዎች ባጠመዱት ወጥመድ ይያዙ። |