መዝሙር 136 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምስጋና መዝሙር 1 ቸር ስለ ሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 2 ከአማልክት ሁሉ ለሚበልጠው አምላክ ምስጋና አቅርቡ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 3 የጌቶች ጌታ ለሆነው አምላክ ምስጋና አቅርቡ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 4 እርሱ ብቻ ታላላቅ ተአምራትን ያደርጋል፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 5 በጥበቡ ሰማያትን ፈጠረ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 6 ምድርን በጥልቅ ውሃዎች ላይ መሠረተ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 7 ታላላቅ ብርሃናትን ፈጠረ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 8 ፀሐይ በቀን እንዲያበራ አደረገ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 9 ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ አደረገ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 10 የግብጻውያንን የበኲር ወንዶች ልጆች ገደለ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 11 የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ አገር መርቶ አወጣ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 12 በኀያልነቱና በሥልጣኑ ይህን አደረገ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 13 ቀይ ባሕርን ከፈለ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 14 እስራኤልንም በመካከሉ አሳለፈ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 15 የግብጽን ንጉሥና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር አሰጠመ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 16 ሕዝቡን በበረሓ መራ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 17 ታላላቅ ነገሥታትን ገደለ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 18 ኀያላን ነገሥታትንም ደመሰሰ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 19 የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን ገደለ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 20 የባሳንንም ንጉሥ ዖግን ገደለ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 21 ምድራቸውን ሁሉ ለሕዝቡ ርስት አድርጎ ሰጠ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 22 ለአገልጋዩ ለእስራኤል አወረሰ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 23 በተሸነፍን ጊዜ አልረሳንም፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 24 ከጠላቶቻችን እጅ ነጻ አወጣን፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 25 ለሥጋ ለባሽ ፍጥረት ሁሉ ምግብን ይሰጣል፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። 26 ይህን ሁሉ ስላደረገ ለሰማይ አምላክ ምስጋና አቅርቡ፤ ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ነው። |