መዝሙር 130 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ከጥልቅ ሐዘን የተነሣ ወደ አንተ እጮኻለሁ። 2 እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ስማ! ምሕረትህን ፈልጌ ስጮኽም አድምጠኝ! 3 ኃጢአታችንን ብትከታተል ማን ከፍርድ ሊያመልጥ ይችላል? 4 ነገር ግን አንተን እንድናከብርህ ኃጢአታችንን ይቅር ትልልናለህ። 5 እግዚአብሔርን በናፍቆት እጠባበቃለሁ፤ በቃሉም እታመናለሁ። 6 ንጋትን ከሚጠባበቁ ጠባቂዎች ይልቅ እኔ እግዚአብሔርን በናፍቆት እጠባበቃለሁ። 7 እስራኤል ሆይ! ፍቅሩ ዘለዓለማዊ ስለ ሆነና ሰዎችንም የማዳን ኀይል ያለው ስለ ሆነ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ። 8 እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን ከኃጢአታቸው ሁሉ ያድናቸዋል። |