መዝሙር 115 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለእግዚአብሔር የሚገባ ምስጋና 1 እግዚአብሔር ሆይ! ስለ እኛ ሳይሆን ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህና ስለ ታማኝነትህ ስምህን አክብረው። 2 ስለምን አሕዛብ “አምላካቸው የት አለ?” ይበሉ? 3 አምላካችን በሰማይ ነው፤ እርሱ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል። 4 እነርሱ የሚያመልኩአቸው ጣዖቶች ግን በሰው እጅ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። 5 አፍ አላቸው፤ አይናገሩም፤ ዐይን አላቸው፤ አያዩም፤ 6 ጆሮ አላቸው፤ አይሰሙም፤ አፍንጫ አላቸው፤ አያሸቱም፤ 7 እጅ አላቸው፤ አይዳስሱም፤ እግር አላቸው፤ አይሄዱም፤ ድምፅም ማሰማት አይችሉም። 8 የሠሩአቸውና የሚታመኑባቸው ሁሉ እንደነዚህ ጣዖቶች ናቸው። 9 እናንተ የእስራኤል ሕዝብ ግን የሚረዳችሁና የሚጠብቃችሁ እግዚአብሔር ስለ ሆነ በእርሱ ታመኑ። 10 እናንተ የእግዚአብሔር ካህናት የአሮን ልጆች የሚረዳችሁና የሚጠብቃችሁ እርሱ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ታመኑ። 11 እናንተ የምትፈሩት ሁሉ የሚረዳችሁና የሚጠብቃችሁ እርሱ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ታመኑ። 12 እግዚአብሔር ያስታውሰናል፤ ደግሞም ይባርከናል፤ የእስራኤልን ሕዝብና የእግዚአብሔርን ካህናት ሁሉ ይባርካል። 13 የሚፈሩትን ሁሉ፥ ታላላቆችንም ሆነ ታናናሾችን ይባርካል። 14 እግዚአብሔር እናንተና ልጆቻችሁ እንድትበዙ ያድርጋችሁ! 15 ሰማይንና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! 16 ሰማይ የእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጥቶአል። 17 ወደ ዝምታ ዓለም፥ ወደ መቃብር የወረዱ ሙታን እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑት አይችሉም። 18 እኛ ግን በሕይወት ያለነው ከአሁኑ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እናመሰግነዋለን። እግዚአብሔር ይመስገን! |