መዝሙር 104 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለፈጣሪ የቀረበ ምስጋና 1 ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እንዴት ታላቅ ነህ! ግርማንና ክብርን ለብሰሃል። 2 ብርሃንንም እንደ ልብስ ተጐናጽፈሃል፤ ሰማይን እንደ ድንኳን ዘርግተሃል። 3 በጠፈር ላይ ካለው ውሃ በላይ ቤትህን ሠርተሃል፤ ደመና ሠረገላህ ነው፤ በነፋስ ክንፎችም ትሄዳለህ። 4 ነፋስ መልእክተኛህ ነው፤ የእሳት ነበልባልም አገልጋይህ ነው። 5 ምድርን በመሠረትዋ ላይ አጽንተህ አቆምሃት፤ ከቶም አትናወጥም። 6 ውቅያኖስን እንደ ልብስ አለበስካት፤ ውሃውም ተራራዎችን ሸፈነ። 7 ውሃውን በገሠጽከው ጊዜ ከፊትህ ሸሸ፤ የትእዛዝህን ድምፅ በሰማ ጊዜ በፍጥነት ሮጠ። 8 አንተ ወዳዘጋጀህለት ስፍራ፥ ወደ ተራራዎች ላይና ወደ ሸለቆዎች ውስጥ ፈሰሰ። 9 ዳግመኛ ምድርን እንዳይሸፍንም የማይጥሰውን ወሰን አበጀህለት። 10 ምንጮች በሸለቆ ውስጥ እንዲፈስሱ፥ ወንዞችም በተራራዎች መካከል እንዲወርዱ አደረግህ። 11 በዚህ ዐይነት የዱር አውሬዎች የሚጠጡት ውሃ ያገኛሉ፤ የሜዳ አህዮችም ጠጥተው ጥማቸውን ያረካሉ። 12 በነዚህም ምንጮችና ወንዞች አጠገብ ባሉት ዛፎች ላይ፥ ወፎች ጎጆአቸውን ሠርተው ያዜማሉ። 13 ከሰማይ ዝናብን በተራሮች ላይ ታወርዳለህ፤ ምድርም በምትሰጣት በረከት ትሞላለች። 14 ሣርን ለእንስሶች ታበቅላለህ፤ አትክልትንም ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲውል ታደርጋለህ፤ በዚህ ዐይነት ሰው ምግብ የሚሆነውን ዘርቶ ይሰበስባል። 15 ስለዚህ ልቡን ደስ የሚያሰኝ የወይን ጠጅ፥ ፊቱን የሚያበራ ዘይትና ብርታት የሚሰጠውን ምግብ ያዘጋጃል። 16 እግዚአብሔር የተከላቸው የሊባኖስ ዛፎች በቂ ዝናብ ያገኛሉ፤ 17 በላያቸውም ወፎች ጎጆዎቻቸውን ይሠራሉ፤ ሸመላዎችም በእነዚያ ዛፎች ላይ መኖሪያቸውን ያበጃሉ። 18 ዋልያዎች በከፍተኛ ተራራዎች ላይ ይገኛሉ፤ ሽኮኮዎችም በተሰነጠቁ አለቶች ውስጥ ይኖራሉ። 19 ጨረቃን የወቅቶች ምልክት እንድትሆን፥ ፀሐይ የሚጠልቅበትን ጊዜ እንዲያውቅ አድርገሃል። 20 አንተ ጨለማን ፈጠርክ፤ ሌሊትም ሆነ፤ በጨለማም የዱር አውሬዎች ሁሉ ይወጣሉ። 21 እግዚአብሔር የሚያዘጋጀውን ምግብ ሲያድኑ የአንበሳ ደቦሎች ያገሣሉ። 22 ፀሐይ በሚወጣበት ጊዜ ሾልከው ይሄዳሉ፤ ተመልሰው በየመኖሪያቸው ውስጥ ይተኛሉ። 23 ከዚህ በኋላ ሰዎች ለሥራ ይሰማራሉ፤ እስከሚመሽም ድረስ ሲሠሩ ይውላሉ። 24 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ብዙ ነገሮችን ፈጥረሃል፤ ሁሉንም በጥበብ አድርገሃል፤ ምድር አንተ በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች። 25 ከቊጥር በላይ በሆኑ ታላላቅና ታናናሽ ሕያዋን ፍጥረቶች የተሞላው ትልቁና ሰፊው ባሕር እነሆ፥ 26 በላዩ መርከቦች ይመላለሳሉ፤ በውስጡም አንተ የፈጠርከው ሌዋታን የተባለ ታላቅ ዘንዶ ይጫወታል። 27 እነዚህ ሁሉ ምግባቸውን በየጊዜው እንድትሰጣቸው ተስፋ የሚያደርጉት አንተን ነው። 28 አንተ ምግብ ስትሰጣቸው እነርሱም ይመገባሉ፤ አንተ እጅህን ስትዘረጋ እነርሱም መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ በልተው ይጠግባሉ። 29 አንተ ስትለያቸው ሁሉም ይደነግጣሉ፤ እስትንፋሳቸውን ስትወስድባቸውም ይሞታሉ፤ ወደ ተገኙበትም ዐፈር ይመለሳሉ። 30 እስትንፋስ ስትሰጣቸው ግን ይፈጠራሉ፤ ለምድርም አዲስ ሕይወት ትሰጣለህ። 31 የእግዚአብሔር ክብር ለዘለዓለም ይኑር! እግዚአብሔር በፈጠረው ነገር ሁሉ ደስ ይበለው። 32 ምድርን ሲመለከት ትንቀጠቀጣለች፤ ተራራዎችን ሲነካ እነርሱም ይጤሳሉ። 33 በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ድረስ ለአምላኬ የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ። 34 ደስታዬ በእርሱ ስለ ሆነ እርሱም በማቀርብለት የተመስጦ ጸሎት ደስ ይበለው። 35 ኃጢአተኞች ከምድር ላይ ይጥፉ! ግፍ አድራጊዎችም ይደምሰሱ! ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! |