Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 102 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በመከራ ላይ ያለ ሰው ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ! የአንተን ርዳታ በመፈለግ ስጮኽም አድምጠኝ!

2 መከራ በሚደርስብኝ ጊዜ ከእኔ አትለይ! አድምጠኝ፤ በምጣራበትም ጊዜ ፈጥነህ ስማኝ!

3 የሕይወት ዘመኔ እንደ ጢስ እየበነነ በማለቅ ላይ ነው፤ ሰውነቴም እንደ እሳት እየነደደ ነው።

4 እንደ ደረቀ ሣር ተሰባብሬ ደቀቅሁ፤ የምግብ ፍላጎቴም ጠፋ።

5 ድምፄን ከፍ አድርጌ በመቃተቴ ከቈዳና ከአጥንት በቀር ሰውነት የለኝም።

6 ብቻውን በበረሓ እንደሚኖር እርኩምና በወና ቤት እንደሚኖር ጒጒት ሆኜአለሁ።

7 እንቅልፍ ከቶ በዐይኔ አይዞርም፤ በቤት ጣራ ላይ እንዳለ ብቸኛ ወፍ ሆኜአለሁ።

8 ጠላቶቼ ዘወትር ይሳለቁብኛል፤ ስሜንም መራገሚያ አድርገው ያነሡታል።

9 ምግቤ ዐመድ ሆኖአል፤ እንባዬም ከምጠጣው ነገር ጋር ተደባልቆአል፤

10 ይህም የሆነው ከፍ ከፍ ካደረግኸኝ በኋላ፥ ከኀይለኛ ቊጣህ የተነሣ ስለ ጣልከኝ ነው።

11 የሕይወቴ ዘመን እንደ ማታ ጥላ ሆኖአል፤ እንደ ሣርም እጠወልጋለሁ።

12 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለዘለዓለም ንጉሥ ነህ፤ ስምህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ገናና ሆኖ ይተላለፋል።

13 ለጽዮን ምሕረት የምታደርግላት ጊዜ ስለ ተቃረበና ጊዜውም አሁን ስለ ሆነ አንተ ትነሣለህ፤ ለእርስዋም ትራራለህ።

14 ድንጋዮችዋ በአገልጋዮችህ ዘንድ የተወደዱ ናቸው፤ ለፍርስራሾችዋ እንኳ ይራራሉ።

15 አሕዛብ የእግዚአብሔርን ስም የምድር ነገሥታትም አንተን ይፈራሉ።

16 እግዚአብሔር ጽዮንን እንደገና በሚሠራበት ጊዜ በክብሩ ይገለጣል።

17 የድኾችን ጸሎት ይሰማል፤ ልመናቸውንም አይንቅም።

18 ገና ያልተወለዱት ሰዎች እንዲያመሰግኑት ይህን እግዚአብሔር ያደረገውን ድንቅ ነገር ለሚመጣው ትውልድ ጻፉ።

19 እግዚአብሔር በላይ ካለው ከቅዱስ ስፍራው ሆኖ ተመለከተ፤ ከሰማይ ወደ ምድር አየ።

20 ይህንንም ያደረገው የእስረኞችን መቃተት ሰምቶ ሞት የተፈረደባቸውንም ነጻ ለማውጣት ነው።

21 ስለዚህ የእግዚአብሔር ስም በጽዮን ይነገራል፤ በኢየሩሳሌምም ይመሰገናል።

22 ይህም የሚሆነው ሕዝቦችና መንግሥታት በአንድነት ተሰብስበው ለእግዚአብሔር በሚሰግዱበት ጊዜ ነው።

23 እግዚአብሔር ገና ወጣት ሆኜ ሳለሁ ደካማ አደረገኝ፤ ሕይወቴንም አሳጠረ።

24 “አምላክ ሆይ! የአንተ ዘመን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ስለ ሆነ ዕድሜዬን ሳላጠናቅቅ በግማሽ ዕድሜዬ አትውሰደኝ” አልኩ።

25 አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።

26 እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ እነርሱ እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያ ትለውጣቸዋለህ፤ ይወገዱማል።

27 አንተ ግን ለዘለዓለም ያው ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።

28 የአገልጋዮችህ ልጆች በሰላም ይኖራሉ፤ ትውልዳቸውም በአንተ ዘንድ ጸንቶ ይኖራል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች