መዝሙር 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! ስለምን እንደዚህ ርቀህ ትቆማለህ? በችግር ጊዜስ ስለምን ትሰወራለህ? 2 ክፉ ሰዎች ይታበያሉ፤ ድኾችንም ያሳድዳሉ፤ ለሌሎች በዘረጉት ወጥመድ ራሳቸው ይጠመዱ። 3 ኃጢአተኛ በክፉ ምኞቱ ይመካል፤ ጌታ ሆይ! እነዚህ ስግብግብ ሰዎች ይጠሉሃል፤ ይሰድቡህማል። 4 ክፉዎች ስለ እግዚአብሔር ግድ የላቸውም በትዕቢታቸውም እግዚአብሔር የለም ብለው ያስባሉ። 5 ክፉ ሰው በሁሉ ነገር ይሳካለታል፤ የእግዚአብሔርን ፍርድ ግን ሊረዳ አይችልም፤ በጠላቶቹም ላይ ይሳለቃል። 6 በሐሳቡ “የሚያነቃንቀኝ የለም፤ ምንም ችግር ሳያጋጥመኝ ሁልጊዜ እደሰታለሁ” ይላል። 7 ንግግሩም በእርግማን፥ በሐሰትና በዛቻ የተሞላ ነው፤ ተንኰልና ክፉ ነገር በአንደበቱ ናቸው። 8 በመንደሮች አጠገብ ይሸምቃል፤ ረዳት የሌላቸውን ደካሞች ይጠባበቃል፤ ንጹሑን ሰው በድብቅ ይገድላል። 9 እርሱም እንደ አንበሳ ተደብቆ ይቈያል፤ ድኾችን ለመያዝ ይሸምቃል፤ እነርሱንም በአሽክላው ይዞ ይጐትታቸዋል። 10 እርሱ መትቶ ይጥላቸዋል፤ ረዳት የሌላቸው ደካሞች ምስኪኖችም የእርሱ ሰለባ ሆነው ይወድቃሉ። 11 ኃጢአተኛ በሐሳቡ፦ “እግዚአብሔር ረስቶአል፤ ፊቱንም ሸፍኖ በፍጹም አያይም!” ይላል። 12 እግዚአብሔር ሆይ፥ ተነሥ! አምላክ ሆይ፥ ኀያል ክንድህን አንሣ! የተጨቈኑትንም ችላ አትበላቸው። 13 ክፉ ሰዎች ለምን አያከብሩህም? ለምንስ በልባቸው “እግዚአብሔር አይቀጣንም” ይላሉ? 14 አምላክ ሆይ! አንተ ግን ችግርንና ጭንቀትን አይተህ ልታስወግዳቸው መፍትሔ ታዘጋጃለህ፤ ችግረኛ ራሱን ለአንተ ይሰጣል፤ አንተም የሙት ልጆችን ትረዳለህ። 15 የኃጢአተኞችንና የክፉ ሰዎችን ኀይል አድክም፤ ከእንግዲህ ወዲያ ክፋትን እንዳያደርጉ በክፉ ሥራቸው ሁሉ ቅጣቸው። 16 እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፤ ለሌሎች አማልክት የሚሰግዱ ሕዝቦች ግን ከምድሩ ይጠፋሉ። 17 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምስኪኖችን ጸሎት ትሰማለህ፤ ልመናቸውንም አድምጠህ ታበረታታቸዋለህ። 18 በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሌሎችን ለማስፈራራት እንዳይችል፥ አንተ ለወላጅ አልባና ለተጨቈኑ ሰዎች ትከላከላለህ። |