ምሳሌ 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ብዙ ጊዜ ተገሥጾ በእምቢተኛነቱ የሚጸና ሰው በድንገት ይሰበራል። ፈውስም አይኖረውም። 2 ደጋግ ሰዎች ሲሾሙ ሕዝቦች ይደሰታሉ፤ ክፉ ሰዎች ሲሾሙ ግን ሕዝቦች ይጨነቃሉ። 3 ጥበብን የሚወድ አባቱ ያስደስታል፤ አመንዝሮችን የሚከተል ግን ሀብቱን ያባክናል። 4 ንጉሥ ፍትሕ እንዳይጓደል በሚያደርግበት ጊዜ ሀገሩን ያረጋጋል፤ ሕዝብን የሚበዘብዝ መሪ ግን ሀገሩን ወደ ጥፋት ያደርሳል። 5 ወዳጆቹን የሚያቈላምጥ ሰው ለእግራቸው ወጥመድ ይዘረጋል። 6 ክፉ ሰው የገዛ ኃጢአቱ ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል፥ ደግ ሰው ግን እየዘመረ ሐሤትን ያደርጋል። 7 ደግ ሰው ስለ ድኾች መብት ይቈረቈራል፤ ክፉ ሰው ግን ለእንደዚህ ዐይነቱ ነገር ግድ አይኖረውም። 8 ለሌሎች ሰዎች ደንታ የሌላቸው ፌዘኞች በከተማ ውስጥ ብጥብጥ ያነሣሣሉ፤ ጠቢባን ግን የደፈረሰውን ጸጥታ መልሰው ያረጋጋሉ። 9 ጥበበኛ ሰው ሞኝን ሰው ከሶ ፍርድ ቤት ቢያቀርብ ሞኙ ሰው በቊጣና በሳቅ ሰላምን ይነሣል። 10 ነፍሰ ገዳዮች ንጹሑን ሰው ይጠላሉ፤ ደጋግ ሰዎችንም ለመግደል ይፈልጋሉ። 11 ሞኝ ሰው የቊጣ ስሜቱን ይገልጣል፤ ጥበበኛ ሰው ግን ቊጣውን በትዕግሥት ይገታል። 12 አንድ መሪ ሐሰተኛ ወሬ የሚቀበል ከሆነ ባለሟሎቹ የሆኑ ባለሥልጣኖች ሁሉ ግፈኞች ይሆናሉ። 13 ለድኻና እርሱንም ለሚጨቊነው ሰው የዐይን ብርሃን የሚሰጠው እግዚአብሔር ስለ ሆነ በብርሃን አጠቃቀም ሁለቱም እኩል ናቸው። 14 አንድ ንጉሥ ለድኾች በቅን የሚፈርድ ከሆነ ለረዥም ዘመን ያስተዳድራል። 15 ልጆችን መገሠጽና መቅጣት ጥበብ እንዲያገኙ ያደርጋል፤ ልጅ ስድ ዐደግ የሆነ እንደ ሆነ ግን እናቱን ያሳፍራል። 16 ክፉ ሰዎች ሥልጣን ሲይዙ ሕግ መተላለፍ ይበዛል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የክፉ ሰዎችን ውድቀት ሳያዩ አይሞቱም። 17 ልጅህን ቅጣ፤ ዕረፍትና ሰላም በማግኘት ደስ ትሰኛለህ። 18 ከእግዚአብሔር የሚገለጥ መመሪያ ባይኖር ሕዝብ መረን ይለቀቃል፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያከብር ሰው ግን የተባረከ ነው። 19 አንድን አገልጋይ በቃል በመገሠጽ ብቻ ለማረም አይቻልም፤ የምትለው ነገር ቢገባው እንኳ አይታዘዝም። 20 ሳያስብ በችኰላ ከሚናገር ሰው ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው። 21 አንድ ባሪያ ከልጅነቱ ጀምሮ ተቀማጥሎ ካደገ መጨረሻው አያምርም። 22 ቊጡ ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ ግልፍተኛም ብዙ በደልን ይፈጽማል። 23 ትምክሕተኛነት ወደ ውድቀት ያደርስሃል፤ ትሑት ከሆንክ ግን ትከበራለህ። 24 ከሌባ ጋር የሚተባበር ራሱን የጠላ ሰው ነው፤ ቢምልም እንኳ እውነትን አይናገርም። 25 ሰውን የሚፈራ ችግር ላይ ይወድቃል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን በሰላም ይኖራል። 26 ብዙ ሰዎች የባለሥልጣንን ርዳታ ይፈልጋሉ፤ ፍትሕ የሚገኘው ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። 27 ክፉ ሰዎች በደጋግ ሰዎች ዘንድ የተጠሉ ናቸው፤ ደጋግ ሰዎችም በክፉ ሰዎች ዘንድ ይጠላሉ። |