Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ኃጢአተኞች ማንም ሳያሳድዳቸው ይሸሻሉ፤ ደግ ሰዎች ግን እንደ አንበሳ ደፋሮች ናቸው።

2 አንድ ሕዝብ ኃጢአተኛ ሲሆን መሪዎች ይለዋወጡበታል፤ ዐዋቂና አስተዋይ መሪ ሲኖረው ግን ለረዥም ጊዜ ጽኑ ሕዝብ ይሆናል።

3 ድኾችን የሚጨቊን መሪ ሰብልን እንደሚያጠፋ ኀይለኛ ዝናብ ነው።

4 ሕግን የማያከብሩ ሰዎች ክፉ ሰዎችን ያመሰግናሉ፤ ሕግን የሚያከብሩ ግን ክፉዎችን ይቃወማሉ።

5 ክፉ ሰዎች ፍትሕ ምን እንደ ሆነ አያውቁም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሰዎች ግን በሙሉ ያስተውሉታል።

6 ሀብታም ሆኖ አታላይ ከመሆን ይልቅ ድኻ ሆኖ ታማኝ መሆን ይሻላል።

7 ሕግን የሚያከብር ልጅ ጥበበኛ ነው፤ ከማይረቡ ወስላቶች ጋር ወዳጅ የሚሆን ልጅ ግን አባቱን ያሳፍራል።

8 በአራጣ በማበደርና ሰዎችን በመበዝበዝ የሚከብር ሰው ሀብቱ ሁሉ ለድኾች ልግሥና ለሚያደርግ ሰው ይተላለፋል።

9 አንድ ሰው ሕግን ባያከብር ጸሎቱ በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ይሆናል።

10 እውነተኛውን ሰው አግባብቶ ወደ ክፉ መንገድ የሚመራ ባጠመደው ወጥመድ ይያዛል፤ ንጹሕ ሰው ግን የመልካም ሥራውን ዋጋ ያገኛል።

11 ሀብታም ሰው ዘወትር ጥበበኛ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ የሆነ ድኻ ግን የእርሱን ጠባይ መርምሮ ያውቃል።

12 ደጋግ ሰዎች ድል በሚያደርጉበት ጊዜ ሰው ሁሉ ይደሰታል፤ ክፉ ሰዎች ሥልጣን በሚይዙበት ጊዜ ግን ሰው ሁሉ በሐዘን አንገቱን ይደፋል።

13 ኃጢአቱን የሚደብቅ ኑሮው አይሳካለትም፤ ኃጢአቱን ተናዝዞ ዳግመኛ ኃጢአት ከመሥራት የሚቈጠብ ግን የእግዚአብሔርን ምሕረት ያገኛል።

14 ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የተባረከ ነው፤ እምቢተኛ የሚሆን ሰው ግን ችግር ላይ ይወድቃል።

15 ድኾችን በጭካኔ የሚገዛ መሪ እንደሚያገሣ አንበሳና ተርቦ ምግቡን ለማደን እንደሚያደባ ድብ ነው።

16 ማስተዋል የጐደለው መሪ ጨካኝ ይሆናል፤ ብዝበዛን የሚጠላ መሪ ግን ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል።

17 አንድ ሰው የሰውን ሕይወት ቢያጠፋ እስኪሞት ድረስ እየሸሸ ይኑር፤ ማንም ሰው አያስጠጋው።

18 ታማኝ ሰው በሰላም ይኖራል፤ ጠማማ ሰው ግን በጒድጓድ ውስጥ ይወድቃል።

19 ትጉህ ገበሬ በቂ ምግብ ይኖረዋል፤ በከንቱ ምኞት የሚመራ ግን እንደ ደኸየ ይኖራል።

20 ታማኝ ሰው የተባረከ ሕይወት ይኖረዋል፤ ሀብታም ለመሆን የሚስገበገብ ሰው ግን ቅጣት ያገኘዋል።

21 አድልዎ ማድረግ አይገባም፤ አንዳንድ ሰው ግን ቊራሽ እንጀራ ለማግኘት ብሎ ያደላል።

22 ስስታም ሀብታም ለመሆን ሲጣደፍ ድኽነት በቶሎ የሚመጣበት መሆኑን አይገነዘብም።

23 ሰውን ከማቈላመጥ ይልቅ እየመከረ የሚገሥጸውን ሰው በመጨረሻ ያመሰግነዋል።

24 ከአባቱና ከእናቱ ሰርቆ “ኃጢአት አላደረግሁም” የሚል ሰው ከማንኛውም አጥፊ ሰው የተሻለ አይደለም።

25 ስስታም ሰው ጠብን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ግን ይበለጽጋል።

26 በራሱ የሚታመን ሰው ሞኝ ነው፤ በጥበብ የሚመራ ሰው ግን በሰላም ይኖራል።

27 ለድኾች የሚሰጥ ከቶ አይቸገርም፤ ድኾችን ላለማየት ዐይኖቹን የጨፈነ ግን በሰዎች ዘንድ የተረገመ ይሆናል።

28 ክፉ ሰዎች ሲሾሙ ሰዎች ይደበቃሉ፤ እነርሱ ሲሻሩ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች