Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


-19-

1 በክፉ ሰዎች አትቅና፤ ከእነርሱም ጋር ጓደኛ ለመሆን አትፈልግ፤

2 እነርሱ ዘወትር በአእምሮአቸው ግፍን ያቅዳሉ፤ በአንደበታቸውም ይሸነግላሉ።


-20-

3 በጥበብ ቤት ይሠራል፤ በማስተዋልም ጸንቶ እንዲኖር ይደረጋል።

4 ዕውቀት ሲኖር ቤት በከበሩና በሚያምሩ ዕቃዎች ይሞላል።


-21-

5 ብርቱ ከመሆን ይልቅ ብልኅ መሆን ይሻላል፤ በእርግጥም ዕውቀት ከኀይል ይበልጣል፤

6 ለጦርነት ከመሰለፍህ በፊት በጥንቃቄ ዕቅድ ማውጣት ይኖርብሃል፤ ብዙ አማካሪዎች የምታገኝ ከሆነም ማሸነፍህ አይቀርም።


-22-

7 ማስተዋል የጐደለው ሰው ጥበብን መገንዘብ አይችልም፤ ሰዎች ቁም ነገር ባለው ጉዳይ ላይ ሲወያዩ እርሱ የሚያቀርበው አስተያየት የለም።


-23-

8 ዘወትር ክፋትን ለማድረግ የሚያሤር ሁሉ “ተንኰለኛ” የሚል የቅጽል ስም ይወጣለታል፤

9 ሞኝ ሁልጊዜ የሚያስበው ኃጢአትን ስለ ማድረግ ነው፤ ፌዘኛን ሰዎች ሁሉ ይጠሉታል።


-24-

10 መከራ በሚደርስብህ ጊዜ መጽናት የማትችል ከሆንክ ምንም ብርታት የለህም ማለት ነው።


-25-

11 በግፍ ወደ ሞት የሚወሰዱትን ሰዎች ታደግ፤ ለመገደል እያዳፉ ከሚወስዱአቸው ሰዎች እጅ አድን።

12 ምናልባት “እኔ አላውቀውም” ትል ይሆናል፤ ነገር ግን ልብን የሚመረምር አያስተውለውምን? እርሱ ሕይወትህን የሚጠብቅ እርሱ አያውቀውምን? እያንዳንዱንስ እንደ ሥራው አይከፍለውምን?


-26-

13 ልጄ ሆይ! መልካም ስለ ሆነ ማር. ብላ፤ የማር ወለላ ለምላስህ ጣፋጭ ነው።

14 ጥበብም ለነፍስህ መልካም መሆኑን ዕወቅ፤ ጥበብን ብታገኝ የወደፊት ኑሮህ የተቃና ይሆናል፤ ተስፋህም አያቋርጥም።


-27-

15 እንደ ዐመፀኛ ሰው የጻድቁን ሰው ቤት ለመዝረፍ አትሸምቅ፤ መኖሪያውንም አትውረር።

16 ጻድቅ ሰው ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ እንደ ገና ይነሣል፤ ዐመፀኞች ግን ጥፋት ይደርስባቸዋል።


-28-

17 ጠላትህ ሲሰናከል ደስ አይበልህ፤ በሚወድቅበትም ጊዜ ሐሤት አታድርግ፤

18 በዚህ ነገር ደስ ቢልህ ግን እግዚአብሔርን ታሳዝናለህ፤ እግዚአብሔርም በጠላትህ ላይ የሚያሳየውን ቊጣ ያቆማል።


-29-

19 በክፉ ሰዎች አድራጎት አትጨነቅ፤ በእነርሱም አትቅና፤

20 ዐመፀኛ ሰው “ወደ ፊት ይህን አገኛለሁ” ብሎ ተስፋ የሚያደርገው ነገር የለውም።


-30-

21 ልጄ ሆይ! እግዚአብሔርን ፍራ ንጉሥንም አክብር፤ በእነርሱም ላይ ከሚያምፁ ሰዎች ጋር አትተባበር።

22 በእነዚህ ዐመፀኞች ላይ ታላቅ ጥፋት ይደርስባቸዋል፤ የሚደርስባቸው ጥፋት ግን ምን ዐይነት እንደ ሆነ ማን ያውቃል?


ተጨማሪ የጥበብ ምክሮች

23 የጥበበኞች ተጨማሪ አባባሎች፦ በዳኝነት ማዳላት ስሕተት ነው፤

24 በደለኛውን ንጹሕ የሚያደርግን ዳኛ፥ ሰዎች ይረግሙታል፤ ሕዝቦችም ያወግዙታል።

25 በደለኛውን በትክክል የሚቀጡ ዳኞች ግን መልካም ይሆንላቸዋል፤ ብዙ በረከትም ያገኛሉ።

26 ትክክለኛ መልስ የሚሰጥ ሰው እንደ ልብ ወዳጅ ይቈጠራል።

27 በመጀመሪያ በርስትህ ላይ ለኑሮህ የሚያስፈልግህን ሁሉ አደራጅ፤ ከዚያ በኋላ ቤት ሥራ።

28 በማንም ሰው ላይ ያለ በቂ ምክንያት አትመስክር፤ በእርሱም ላይ አሳሳች ቃል አትናገር።

29 “ሰው ክፉ ነገር በሚያደርግብኝ መጠን እኔም ክፉ ነገር አደርግበታለሁ! የበቀል ብድራቴንም እመልሳለሁ!” አትበል።

30 በሰነፍና ማስተዋል በጐደለው ሰው እርሻ ውስጥ በወይኑም አትክልት ቦታ ሄድኩኝ፤

31 በአረምና በቊጥቋጦ ተሞልቶ ነበር፤ በዙሪያውም ያለ የግንብ አጥር ፈርሶአል።

32 ይህን በተመለከትኩ ጊዜ ስለ እርሱ አስባለሁ፤ ከተመለከትኩትም ነገር ትምህርትን ገበየሁ።

33 ብትፈልግ ትንሽ ሸለብ ያድርግህ፤ ጥቂት እንቅልፍም ይውሰድህ፤ እጆችህንም አጣምረህ ለጥቂት ጊዜ ዐረፍ በል።

34 ነገር ግን ገና ተኝተህ ሳለህ ድኽነትና ማጣት የጦር መሣሪያ እንደ ታጠቀ ወንበዴ በድንገት እንደሚደርሱብህ ዕወቅ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች