ምሳሌ 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ራስ ወዳድ ሰው የራሱን ምኞት ብቻ ይከተላል፤ ከሌላ ሰው የሚቀርብ ትክክለኛ አስተሳሰብን እንኳ ይቃወማል። 2 ሞኝ የራሱን አስተያየት ብቻ መግለጥ ይፈልጋል እንጂ ዕውቀትን ከሌላ ሰው መገብየት ደስ አያሰኘውም። 3 ኃጢአትና ውርደት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው፤ ክብርህን ብታጣ በምትኩ የምታገኘው ውርደት ነው። 4 ከሰው አንደበት የሚወጣው የጥበብ ንግግር እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ እንደ ምንጭ ውሃም ጣፋጭ ነው። 5 ለበደለኛው ማዳላትና ንጹሕ ሰው ትክክለኛ ፍትሕ እንዳያገኝ ማድረግ ተገቢ አይደለም። 6 የሞኝ ንግግር ጠብን ያነሣሣል፤ ልፍለፋውም በትርን ይጋብዛል። 7 ሞኝ በሚናገርበት ጊዜ ራሱን በጒዳት ላይ ይጥላል፤ አነጋገሩም ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል። 8 የሐሜተኛ ሰው ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሰኘ እስከ ውስጥ ሰውነት ድረስ ይወርዳል። 9 ሰነፍ ሰው ከአጥፊ ሰው ተለይቶ አይታይም፤ 10 የእግዚአብሔር ስም እንደ ጠንካራ ምሽግ ነው፤ ስለዚህ ደጋግ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ይድናሉ። 11 ሀብታሞች ግን ሀብታቸው በከተማ ዙሪያ እንዳለ ከፍተኛና ጠንካራ ግንብ የሚጠብቃቸው ይመስላቸዋል። 12 ትዕቢት ጥፋትን ያመጣል፤ ትሕትና ግን ክብርን ያጐናጽፋል። ክብርን ግን ትሕትና ይቀድመዋል። 13 ሳያዳምጡ መልስ መስጠት፥ ሞኝ ያደርጋል፤ አሳፋሪም ነው። 14 ጠንካራ መንፈስ ሕመምን ያስታግሣል፤ መንፈሱ የደከመውን ግን ማንም አይረዳውም። 15 የጥበበኛ ሰው ልብ ዕውቀትን ገንዘብ ያደርጋል፤ የአስተዋዮችም ጆሮ ጥበብን ይፈልጋል። 16 ስጦታ ለሰጪው መንገድን ይከፍትለታል፤ ወደ ትልልቆች ሰዎችም ፊት መቅረብ ያስችለዋል። 17 በአደባባይ በመጀመሪያ ቀርቦ የሚናገር ሰው ተከራካሪው መጥቶ ጥያቄ እስከሚያቀርብለት ድረስ፥ ዘወትር እርሱ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስለዋል። 18 ዕጣ መጣል ጠብን ያበርዳል፤ ሁለት ጠንካራ ተከራካሪዎችንም ይገላግላል። 19 ወንድምህን እርዳው፤ እርሱም በከተማ ዙሪያ እንዳለ ጠንካራ ግንብ ይጠብቅሃል፤ ከእርሱ ጋር ብትጣላ ግን በሩን ይዘጋብሃል። 20 ሰው በሚናገረው የንግግር ውጤት በመርካት ተደስቶ ይኖራል። 21 አንደበትህ ሕይወትህን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል፤ ስለዚህ በአንደበትህ ወዳጆችን ብታፈራ ተደስተህ ትኖራለህ። 22 ሚስት ከእግዚአብሔር የምትሰጥ በረከት ስለ ሆነች ሚስት ካገኘህ መልካም ነገር አግኝተሃል ማለት ነው፤ 23 ድኻ እየተለማመጠ በትሕትና ይናገራል፤ ሀብታም ግን በትምክሕት ይመልሳል። 24 ወዳጆች ሳይሆኑ ወዳጆች መስለው የሚታዩ አሉ፤ እውነተኛ ወዳጅ ግን ከወንድም ይበልጣል። |