Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ሰው ዕቅድ ያወጣል፥ ነገር ግን ዕቅዱ በሥራ ላይ የሚውለው እግዚአብሔር ይሁን ብሎ ሲፈቅድ ብቻ ነው።

2 ሰው የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል የሆነ ሊመስለው ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ዓላማውን ይመዝናል።

3 የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል።

4 እግዚአብሔር የፈጠረው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው፤ የክፉዎችም መጨረሻ ጥፋት ነው።

5 እግዚአብሔር ትምክሕተኞችን ሁሉ ይጸየፋል፤ ከቅጣት እንዲያመልጡም አያደርጋቸውም።

6 በፍቅርና በእምነት ኃጢአት ይሰረያል፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፉ ነገር ይርቃል።

7 ሰው በአካሄዱ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከሆነ ከጠላቶቹ ጋር እንኳ በሰላም እንዲኖር ያደርገዋል።

8 ፍትሕን በማጓደል ከሚገኝ ብዙ ሀብት ይልቅ በእውነት የሚገኝ ጥቂት ነገር ይሻላል።

9 ሰው ዕቅድ ያወጣል፤ ነገር ግን ዕቅዱ ከግቡ የሚደርሰው በእግዚአብሔር ርዳታ ነው።

10 ንጉሥ የሚፈርደው ከእግዚአብሔር በተቀበለው ሥልጣን ነው፤ ስለዚህ ውሳኔዎቹ ዘወትር ትክክል ናቸው።

11 ሚዛንና መስፈሪያ ትክክል እንዲሆኑ፥ ለሽያጭ የሚቀርቡት ዕቃዎች ሁሉ ሚዛናቸው የተስተካከለ እንዲሆን የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው።

12 መንግሥት የሚጸናው በፍትሕ ስለ ሆነ ክፉ ሥራ በመሪዎች ዘንድ የተጠላ ነው።

13 ነገሥታት በእውነተኛ ንግግር ይደሰታሉ፤ እውነት የሚናገረውንም ሰው ያከብራሉ።

14 የንጉሥ ቊጣ የሞት መልእክተኛ ነው። ብልኅ ሰው ግን ቊጣውን ያበርዳል።

15 የንጉሥ ፈገግታ ሕይወት ነው፤ ከእርሱም ተወዳጅነትን ማግኘት እንደ በልግ ዝናብ ልምላሜን ይሰጣል።

16 ወርቅን ከማግኘት ጥበብን ማግኘት ይበልጣል፤ ብርንም ከማግኘት ዕውቀትን ማግኘት ይሻላል።

17 ደጋግ ሰዎች ክፋት በሌለበት መንገድ ይሄዳሉ፤ አካሄዱን የሚያሳምር ሕይወቱን ይጠብቃል።

18 ትዕቢት ወደ ጥፋት ይወስዳል፤ ትምክሕተኛነትም ወደ ውድቀት ያደርሳል።

19 ከትዕቢተኞች ጋር የዘረፉትን አብሮ ከመካፈል ትሑት ሆኖ በድኽነት መኖር ይሻላል።

20 ለሚሰጠው ምክር ትኲረትን የሚሰጥ ይበለጽጋል፤ በእግዚአብሔርም የሚተማመን የተባረከ ነው።

21 በአስተሳሰብ መብሰል ጥበበኛነትን ያመለክታል፤ ጣዕም ባለው አነጋገር መናገር ሌሎችን ያስተምራል።

22 ጥበብን ገንዘብ ላደረጋት የሕይወት ምንጭ ናት፤ ሞኞች ግን በሞኝነታቸው ይቀጣሉ።

23 የጥበበኛ ሰው አእምሮ ንግግሩን ይቈጣጠራል፤ ከአፉም የሚወጣው ንግግር ትምህርትን ያስፋፋል።

24 መልካም ንግግር እንደ ማር. ወለላ ይጣፍጣል፤ ለሰውነትም ፈውስ የሚሰጥ ነው።

25 ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ያመራል።

26 ሰውን ጠንክሮ እንዲሠራ የሚያደርገው የምግብ ፍላጎቱ ነው፤ ራብ ደግሞ ለሥራ ይገፋፋዋል።

27 ወንበዴ ክፉ ነገርን ያቅዳል ንግግሩም እንደ እሳት ያቃጥላል።

28 ተንኰለኛ ሰው ጠብን ይዘራል፤ ሐሜተኛም የቅርብ ወዳጆችን እንዲለያዩ ያደርጋል።

29 ዐመፀኛ ሰውን ያታልላል፤ ወደ ጥፋትም ይመራል።

30 ዐይኑን በሰው ላይ የሚጠቅስ ተንኰልን ያቀደ ነው፤ ከንፈሩንም የሚነክስ ወደ ክፋት የሚያመራ ነው።

31 ሽበት የክብር ዘውድ ነው። የሚገኘውም በተቀደሰ አኗኗር ነው።

32 ኀይለኛ ከመሆን ይልቅ ታጋሽ መሆን ይሻላል፤ ብዙ ከተሞችን በጦርነት ድል ነሥቶ ከመያዝ ይልቅ ራስን መቈጣጠር ይበልጣል።

33 ሰዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ ዕጣ ይጥላሉ፤ ነገር ግን ውሳኔውን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች