ዘኍል 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመብራቶቹ አቀማመጥ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ሰባቱን መብራቶች በመቅረዙ ላይ በሚያኖርበት ጊዜ ብርሃኑ ፊት ለፊት እንዲበራ አድርጎ ያስቀምጣቸው ዘንድ ለአሮን ንገረው።” 3 እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አሮንም እንዲህ አደረገ፤ በመቅረዙ ፊት ለፊት እንዲበሩ በማድረግም መብራቶቹን አኖረ። 4 መቅረዙም እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ዕቅድ መሠረት እስከ አገዳውና አበባው ድረስ ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ነበር። የሌዋውያን የመንጻትና የመቀደስ ሥርዓት 5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 6 “ከቀሩት የእስራኤል ሕዝብ መካከል ሌዋውያንን ለይተህ እንዲነጹ አድርግ፤ 7 ለመንጻት ሥርዓት በተዘጋጀው ውሃ እርጫቸው፤ በሰውነታቸው ላይ ያለውን ጠጒር ሁሉ እንዲላጩና ልብሳቸውንም አጥበው ራሳቸውን እንዲያነጹ አድርግ፤ 8 ቀጥሎም አንድ ወይፈንና ለእህል ቊርባን የተመደበውን በዘይት የተለወሰ ዱቄት ይውሰዱ፤ አንተም ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚቀርብ አንድ ወይፈን ውሰድ፤ 9 ከዚያን በኋላ የእስራኤልን ሕዝብ ሰብስበህ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ፊት እንዲቆሙ አድርግ። 10 እስራኤላውያን እጆቻቸውን በሌዋውያን ራስ ላይ ይጫኑ፤ 11 ሌዋውያን ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ለእኔ ለእግዚአብሔር እንደ ልዩ ስጦታ ሆነው በመቅረብ ያገለግሉኝ ዘንድ አሮን ይቀድሳቸዋል። 12 ከዚህ በኋላ ሌዋውያን እጆቻቸውን በሁለቱ ኰርማዎች ላይ ይጭናሉ፤ አንዱ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ ሌላው የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል፤ ለሌዋውያን ለማስተስረይ የሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት በዚህ ዐይነት ይከናወናል።” 13 “ሌዋውያንን ለእኔ የተለየ ስጦታ አድርገህ ቀድስልኝ፤ አሮንንና ልጆቹንም በእነርሱ ላይ ሹማቸው፤ 14 በዚህም ዐይነት ሌዋውያን የኔ ይሆኑ ዘንድ ከቀሩት የእስራኤል ሕዝብ መካከል ለይልኝ፤ 15 ካነጻሓቸውና ከቀደስካቸውም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ብቃት ይኖራቸዋል። 16 እኔ እነርሱን በኲር ሆነው ለሚወለዱት ለእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ሁሉ ምትክ አድርጌ ስለ መረጥኳቸው የእኔ ብቻ ይሆናሉ። 17 በግብጽ ምድር በኲር ሆኖ የተወለደውን በገደልኩ ጊዜ ከእያንዳንዱ እስራኤላዊ ቤተሰብ በኲር ሆኖ የተወለደውንና የእንስሶችንም በኲር ሁሉ ለእኔ የተለየ እንዲሆን ቀድሼው ነበር። 18 እነሆ፥ አሁን ግን ስለ እስራኤላውያን በኲር ልጆች ምትክ ሌዋውያንን ለይቻለሁ፤ 19 የእስራኤልን ሕዝብ ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግሉና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ በመቅረብ እንዳይቀሠፉ ይጠብቁአቸው ዘንድ፥ ሌዋውያንን ከእስራኤላውያን እንደ ስጦታ ተቀብዬ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻለሁ።” 20 ስለዚህ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፥ ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሌዋውያንን ቀደሱ። 21 ሌዋውያንም ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ አድርጎ ለእግዚአብሔር ለያቸው የመንጻቱንም ሥርዓት ፈጸመላቸው፤ 22 እግዚአብሔር ለሙሴ ስለ ሌዋውያን በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሕዝቡ ሁሉን ነገር አደረጉ፤ በዚህም ዐይነት ሌዋውያን በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ዝግጁዎች ሆኑ። 23 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “ኻያ አምስት ዓመት የሞላውና ከዚያም በላይ የሆነ ሌዋዊ ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቱን ይፈጽማል፤ 25 ኀምሳ ዓመት ሲሞላላቸው የአገልግሎት ሥራቸውን ይተዋሉ፤ ከዚያም በኋላ አይሠሩም። 26 ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚፈጽሙት አገልግሎት እንደ ረዳት ሆነው ይሠራሉ፤ እነርሱ ራሳቸው ብቻቸውን ግን ምንም ዐይነት ሥራ አይሥሩ፤ እንግዲህ የሌዋውያንን አገልግሎት ሥርዓት የምታስይዘው በዚህ ዐይነት ነው።” |