Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 በለዓምም እነሆ፥ እስራኤልን መመረቅ እግዚአብሔርን እንዳስደሰተው ስለ ተረዳ ከዚህ በፊት እንዳደረገው የሟርት ምልክት መከተል አላስፈለገውም፤ ፊቱንም ወደ በረሓው መለሰ።

2 የእስራኤል ሕዝብ በየነገዳቸው በቅደም ተከተል ተራ ሰፍረው አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ስላደረበት፥

3 እንዲህ ሲል ትንቢት ተናገረ፤ “የቢዖር ልጅ በለዓም የሚናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፤ እርሱም ሁሉን ነገር በግልጥ ማየት የሚችልና፥

4 የእግዚአብሔርን ቃላት የሚሰማ፥ ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ተከፍተው፥ ሁሉን የሚችል አምላክን ራእይ የሚያይ ሰው መልእክት ይህ ነው።

5 ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ፥ የሰፈርክባቸው ቦታዎች ምንኛ ያምራሉ?

6 እነርሱም እንደ ተዘረጉ ሸለቆዎችና፥ በወንዝ ዳር እንደሚገኙ የአትክልት ቦታዎች፥ እግዚአብሔር እንደ ተከለው የሬት ዛፍ ወይም በውሃ ዳር እንደ በቀለ የሊባኖስ ዛፍ ናቸው።

7 ዝናብ ዘወትር ስለሚዘንብላቸው ማድጋቸው ሁልጊዜ ሙሉ ነው አዝመራቸውም በቂ ውሃ አለው፤ ንጉሣቸው ከአጋግ የሚበልጥ ይሆናል፤ መንግሥቱም ከፍ ከፍ ይላል።

8 ከግብጽ ያወጣቸው እግዚአብሔር ለእነርሱ እንደ ጐሽ ይዋጋላቸዋል፤ ጠላቶቻቸው የሆኑትን ሕዝቦች ይቦጫጭቅላቸዋል፤ አጥንቶቻቸውን ያደቃል፤ ቀስቶቻቸውንም ይሰባብራል።

9 ይህ ሕዝብ፥ ለመያዝ እንደ ተዘጋጁ ወንድ አንበሳና ሴት አንበሳ አድብቶአል፤ በተኛ ጊዜ ሊያስነሣው የሚደፍር ማነው? የሚመርቅህ የተመረቀ ይሁን፤ የሚረግምህም የተረገመ ይሁን።”

10 ባላቅ በቊጣ እጆቹን ጨብጦ በለዓምን እንዲህ አለው፤ “እኔ ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠርቼህ ነበር፤ አንተ ግን ስትመርቃቸው ይኸው ሦስተኛ ጊዜህ ነው።

11 እንግዲህስ በቶሎ ወደ ቤትህ ሂድ! እኔ በርግጥ ብዙ ዋጋ ልከፍልህ ቃል ገብቼልህ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ዋጋ እንዳታገኝ እግዚአብሔር ዘግቶብሃል።”

12 በለዓምም እንዲህ ሲል ለባላቅ መለሰለት፦ “ወደ እኔ ልከሃቸው ለነበሩ ሰዎች፦

13 ‘ባላቅ በቤተ መንግሥቱ ያለውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝ እንኳ በራሴ ፈቃድ ደግ ወይም ክፉ ነገር አደርግ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል መተላለፍ አልችልም፤ የምናገረው እግዚአብሔር እንድናገር የነገረኝን ነገር ብቻ ነው’ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን?”


በለዓም የተናገረው አራተኛው የትንቢት ቃል

14 በመጨረሻም በለዓም ባላቅን “እነሆ፥ እኔ ወደ ራሴ ሕዝብ ተመልሼ መሄዴ ነው፤ ነገር ግን ከመሄዴ በፊት የእስራኤል ሕዝብ ወደ ፊት በሕዝብህ ላይ የሚያደርጉትን በመግለጥ ላስጠነቅቅህ እወዳለሁ” ካለው በኋላ፥

15 ትንቢቱንም እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ። “ዐይኑ በግልጥ የሚያይለት፥ የቢዖር ልጅ በለዓም የሚናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው፦

16 የግዚአብሔርን ቃል የሚሰማው ሰው የትንቢት ቃል ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ተከፍተው ሁሉን የሚችል አምላክን ራእይ የሚያይ ሰው መልእክት ይህ ነው።

17 አየዋለሁ፤ ነገር ግን አሁን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፤ ግን በቅርብ አይደለም፤ ኮከብ ከያዕቆብ፥ በትረ መንግሥት ከእስራኤል ይወጣል። የሞአብን ድንበር፥ የሴትንም ዘሮች ሁሉ ይደመስሳል።

18 ኤዶምን አሸንፎ የራሱ ያደርጋታል፤ ጠላቱ ሴርም የእርሱ ትሆናለች፤ እስራኤል ድል አድራጊ እንደ ሆነ ይኖራል።

19 ከያዕቆብ አንድ ገዢ ይወጣል፤ በከተማም ውስጥ የተረፉትን ጠራርጎ ያጠፋል።”

20 ከዚህ በኋላ በለዓም ወደ ዐማሌቅ በመመልከት እንዲህ ሲል ይህን የትንቢት ቃል ተናገረ፦ “ዐማሌቅ ከሁሉ የሚበልጥ ኀያል ሕዝብ ነበረ፤ በመጨረሻ ግን እርሱ ራሱ ለዘለዓለም ይጠፋል።”

21 ወደ ቄናውያን መለስ ብሎ የሚከተለውን የትንቢት ቃል ተናገረ፦ “መኖሪያህ አስተማማኝ ቢመስልና፥ ጎጆህም በተራራው ቋጥኝ ውስጥ ቢሆን፥

22 እናንተ ቄናውያን፥ አሦር ድል ነሥታ በምትማርካችሁ ጊዜ ትደመሰሳላችሁ።”

23 በመጨረሻም በለዓም የሚከተለውን የትንቢት ቃል ተናገረ፤ “በሰሜን በኩል የተሰበሰበ ይህ ሕዝብ ማን ነው?

24 ወራሪዎች በመርከብ ከቆጵሮስ ይመጣሉ፤ እነርሱም አሦርንና ዔቤርን ያጠፋሉ፤ እነርሱም ራሳቸው ለዘለዓለም ይጠፋሉ።”

25 ከዚያም በኋላ በለዓም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ባላቅም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች