ሚክያስ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእስራኤል ሕዝብ የሞራል ውድቀት 1 የመከር ፍሬ ተሰብስቦ የወይኑም ቃርሚያ ከተቃረመ በኋላ ሊበላ የሚፈልገውን የወይን ዘለላ እንደማያገኝ ሰው ስለ ሆንኩ ወዮልኝ! እኔ የምመኘውም አስቀድሞ የደረሰው የበለስ ፍሬ የለም። 2 ከምድሪቱ ላይ ታማኝ ሰው ጠፍቶአል፤ አንድም ትክክለኛ ሰው የለም፤ ሁላቸውም ሰውን ለመግደል ያደባሉ፤ እርስ በርሳቸውም አንዱ ሌላውን ተከታትሎ ያጠምዳል። 3 እጆቻቸው ክፉ ነገርን ለማድረግ የተለማመዱ ናቸው፤ ባለ ሥልጣኑና ዳኛው ጉቦ ይጠይቃሉ፤ ኀይለኛ ፍላጎቱን በግዴታ ተግባራዊ ያስደርጋል፤ በዚህም ዐይነት ሁሉም ፍርድን ያጣምማሉ። 4 ከእነርሱ መካከል እጅግ የተሻለ ነው የተባለው ሰው እንደ አሜከላ ነው፤ እጅግ ትክክለኛ ነው የተባለው እንደ ኲርንችት ነው፤ በነቢያቱ አማካይነት ባስጠነቀቃቸው መሠረት እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ እነሆ አሁንም ቢሆን በሽብር ላይ ይገኛሉ። 5 በሰው ላይ እምነትህን አትጣል፤ በቅርብ ወዳጅህም አትተማመን፤ አቅፈሃት ለምትተኛው ሚስትህ የምትናገረው ቃል እንኳ ጥንቃቄ የተሞላበት ይሁን። 6 በዚያን ዘመን ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃል፤ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ ምራትም በዐማትዋ ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ። 7 እኔ ግን እግዚአብሔርን ተስፋ አደርጋለሁ፤ የሚያድነኝን አምላክ እጠባበቃለሁ፤ እርሱም ይሰማኛል። ደኅንነት ከእግዚአብሔር ነው 8 ጠላቴ ሆይ! እኔ ብወድቅም እንኳ እንደገና እነሣለሁና በእኔ ደስ አይበልህ፤ አሁን በጨለማ ውስጥ ብሆንም እግዚአብሔር ያበራልኛል። 9 እግዚአብሔርን በድዬዋለሁ፤ ስለዚህም እርሱ የቀረበብኝን ክስ ተመልክቶ እስኪፈርድልኝ ድረስ ቊጣውን እታገሣለሁ፤ በመጨረሻም እርሱ ወደ ብርሃን ያወጣኛል፤ ፍትሕንም ይሰጠኛል። 10 ጠላቴም ይህን ሁሉ ያያል፤ “አምላክህ እግዚአብሔር የት አለ?” ይለኝ የነበረው ጠላቴ ኀፍረትን ይከናነባል፤ እኔ የጠላቴን ውድቀት አያለሁ፤ በመንገድ ዳር እንዳለ ጭቃ ሲረገጥም እመለከታለሁ። 11 እናንተ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የከተማይቱ ቅጽሮች የሚሠሩበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ግዛታችሁ ይሰፋል። 12 በዚያን ጊዜ ሕዝባችሁ ወደ እናንተ ይመለሳል፤ ይኸውም በስተ ምሥራቅ ከአሦር፥ በስተ ደቡብ ከግብጽ፥ ከኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ፥ እንዲሁም ከሩቅ ባሕሮችንና ተራራዎችን አቋርጠው ይመጣሉ። 13 ምድሪቱ ግን ከሚኖሩባት ሰዎች ክፋት የተነሣ ባድማ ትሆናለች። እግዚአብሔር ለእስራኤል ያሳየው ርኅራኄ 14 እግዚአብሔር ሆይ! የአንተ መንጋ የሆነውን ሕዝብህን በሥልጣንህ ጠብቅ፤ እነርሱም በለመለመ አትክልት ቦታ መካከል በጫካ ውስጥ ብቻቸውን የሚኖሩ ናቸው፤ እንደ ቀድሞው ዘመን በባሳንና በገለዓድ እንዲመገቡ አድርጋቸው። 15 ከግብጽ ምድር ባወጣኸን ጊዜ እንዳደረግኸው ተአምራትን አሳየን። 16 ኀይል ያላቸው ቢሆኑም ይህን አይተው ያፍራሉ፤ እጆቻቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፤ ጆሮዎቻቸውንም ይደፍናሉ። 17 እንደ እባብና እንደ ሌሎችም ተንፏቃቂ ፍጥረቶች ትቢያ ይልሳሉ፤ ከምሽጎቻቸው ወጥተው እየተንቀጠቀጡ ይመጣሉ፤ በፍርሃትም ወደ አንተ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ አንተንም እየፈሩ ይኖራሉ። 18 ኃጢአትን ይቅር የሚል፥ በቀሪውም ሕዝቡ ላይ በደልን የማይቈጥር እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረት ማድረግ ስለሚያስደስትህ ቊጣህ ለዘለዓለም የሚቈይ አይደለም። 19 እንደገና ትራራልናለህ፤ በደላችንን በእግርህ ሥር ጥለህ ትረግጣለህ፤ ኃጢአታችንንም ሁሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለህ። 20 ለቀደሙ አባቶቻችን በማልክላቸው መሠረት ለአብርሃምና ለያዕቆብ ዘር ታማኝነትህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ታሳያለህ። |