Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢያሱ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የገባዖን ሰዎች ኢያሱን ማታለላቸው

1 ከዮርዳኖስ ማዶ በተራራማውና በቈላማው አገሮች፥ በሜዲቴራኒያን ባሕር ጠረፍ፥ እስከ ሊባኖስ ድረስ ያሉት የሒታውያን፥ የአሞራውያን፥ የከነዓናውያን፥ የፔሩዛውያን የኤዊያውያንና የኢያቡሳውያን ነገሥታት ይህን በሰሙ ጊዜ፥

2 ኀይላቸውን በአንድነት አስተባብረው በኢያሱና በእስራኤላውያን ላይ ለመዝመት መጡ።

3 የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በዐይ ከተማዎች ላይ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰሙ፤

4 እርሱን ለማታለል ወሰኑ፤ እነርሱም ስንቃቸውን አዘጋጅተው፥ አሮጌ ስልቻና ቀዳዳው ተለጥፎ የተሰፋ የወይን ጠጅ አቁማዳ በአህዮች ጫኑ፤

5 ተቀዳዶ ያለቀ አሮጌ ልብስ ለብሰው፥ የተጠጋገነ እላቂ ጫማ አደረጉ፤ ለስንቅ የያዙትም እንጀራ ደረቅና የሻገተ ነበር።

6 ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጌልገላ ወደሚገኘው ሰፈር ሄደው ኢያሱንና እስራኤላውያንን፦ “እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ የመጣነውም ከእናንተ ጋር የቃል ኪዳን ውል ለማድረግ ነው” አሉአቸው።

7 የእስራኤል ሰዎች ግን የገባዖንን ሰዎች “ከእናንተ ጋር እንዴት ውል እናደርጋለን? ምናልባትም እናንተ በእኛ መካከል የምትኖሩ ልትሆኑ ትችላላችሁ” አሉአቸው።

8 የገባዖንም ሰዎች ኢያሱን “እኛ አገልጋዮችህ ነን” አሉት። ኢያሱም “እናንተ እነማን ናችሁ? የመጣችሁትስ ከየት ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

9 እነርሱም ይህን ታሪክ ነገሩት፤ “አምላካችሁ እግዚአብሔር በግብጽ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰማን እኛ የመጣነው በጣም ሩቅ ከሆነ አገር ነው፤

10 እንዲሁም ከዮርዳኖስ ማዶ በስተምሥራቅ በነበሩት በሁለቱ አሞራውያን ነገሥታት ላይ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል፤ እነዚህም ሁለቱ ነገሥታት በዐስታሮት ይኖሩ የነበሩት የሐሴቦን ንጉሥ ሲሖንና የባሳን ንጉሥ ዖግ ናቸው።

11 መሪዎቻችንና በምድራችን የሚኖሩት ሕዝቦች ሁሉ ለመንገዳችን የሚሆነንን ስንቅ አዘጋጅተን መጥተን ከእናንተ ጋር እንድንገናኝ ልከውናል፤ ለእናንተ የምንታዘዝ አገልጋዮች እንድንሆንና እናንተም ከእኛ ጋር የሰላም ውል እንድታደርጉ እንጠይቃችሁ ዘንድ አዘውናል።

12 የያዝነውን ስንቅ ተመልከቱ! ከቤት ተነሥተን ከእናንተ ጋር ለመገናኘት ጒዞ ስንጀምር ገና ትኩስ እንጀራ ነበር፤ አሁን ግን ደረቅና የሻገተ መሆኑን ተመልከቱ!

13 እነዚህንም የወይን አቁማዳዎች በሞላናቸው ጊዜ ገና አዲስ ነበሩ፤ አሁን ግን የተቀደዱ መሆናቸውን ተመልከቱ! ከጒዞው ርቀት የተነሣ እነሆ፥ ልብሳችንም ጫማችንም አልቆአል።”

14 የእስራኤልም ሰዎች ከመንገደኞቹ ስንቅ ጥቂት ወሰዱ፤ ስለ ሁኔታው ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ አልጠየቁም።

15 ስለዚህም ኢያሱ ከእነርሱ ጋር ለሕይወታቸው ዋስትና ቃል ኪዳን በመግባት የሰላም ስምምነት አደረገ። የእስራኤል ሕዝብ መሪዎችም ስምምነቱን ለመጠበቅ ቃል ገቡላቸው።

16 ስምምነቱ በተደረገ በሦስተኛውም ቀን እነዚህ ሰዎች ጐረቤቶቻቸው መሆናቸውንና በመካከላቸውም እንደሚኖሩ ሰሙ፤

17 ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ጒዞ ጀምረው ከሦስት ቀን በኋላ እነዚህ ሕዝብ ወደሚኖሩባቸው ከተሞች ደረሱ፤ ከተሞቻቸውም ገባዖን፥ ከፊራ፥ በኤሮትና ቂርያትይዓሪም ተብለው ይጠሩ ነበር፤

18 የሕዝቡ መሪዎች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ምለውላቸው ስለ ነበረ እስራኤላውያን እነርሱን አልገደሉአቸውም። ስለዚሁም ጉዳይ እስራኤላውያን ሁሉ በመሪዎቻቸው ላይ አጒረመረሙ፤

19 መሪዎቹ ግን እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ “በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ቃል ገብተንላቸዋል፤ ስለዚህም አሁን ጒዳት ልናደርስባቸው አይገባም፤

20 ለእነርሱ የምናደርገው እንደዚህ ነው፦ ለእነርሱ ስለማልንላቸው መሐላ የእግዚአብሔር ቊጣ እንዳይደርስብን በሕይወት እንዲኖሩ እንተዋቸው።

21 መሪዎቹም ስለ እነርሱ በወሰኑት መሠረት፦ ይኑሩ፤ ነገር ግን ለመላው ማኅበር እንጨት በመልቀምና ውሃ በመቅዳት ያገልግሉ” አሉ።

22 ኢያሱም የገባዖንን ሕዝብ ወደ እርሱ ፊት እንዲቀርቡ አድርጎ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “በዚሁ በቅርብ የምትኖሩ ሲሆን፥ በጣም ሩቅ ከሆነ አገር የመጣን ነን ብላችሁ ስለምን አታለላችሁን?

23 ይህን በማድረጋችሁ ምክንያት እግዚአብሔር ፈርዶባችኋል፤ ስለዚህም የእናንተ ሕዝብ እንጨት በመቊረጥና ውሃ በመቅዳት ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለዘለዓለም አገልጋዩ ይሆናል።”

24 እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ጌታችን ሆይ! እኛ አገልጋዮችህ በእርግጥ ይህን አድርገናል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እናንተ በውስጧ የሚኖሩትን ሕዝብ በመግደል ምድሪቱን ያወርሳችሁ ዘንድ አገልጋዩን ሙሴን ያዘዘው መሆኑን ዐውቀናል፤ ይህንንም ያደረግነው እናንተን ከመፍራታችን የተነሣ ሕይወታችንን ለማትረፍ ፈልገን ነው።

25 እነሆ፥ አሁን በእናንተ ሥልጣን ሥር ነን፤ መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግብን።”

26 ስለዚህም ኢያሱ፥ ከእስራኤል ሕዝብ ወገን ማንም እንዳይገድላቸውና ተጠብቀው እንዲኖሩ አደረገ።

27 ነገር ግን በዚሁ ጊዜ እንጨት በመቊረጥና ውሃ በመቅዳት ለእስራኤል ሕዝብና ለእግዚአብሔር መሠዊያ አገልጋዮች እንዲሆኑ አደረገ። እነርሱም እስከ አሁን ድረስ እግዚአብሔር ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ቦታ፥ ይህንኑ አገልግሎት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች