Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢያሱ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዐይ ከተማ መያዝና መደምሰስ

1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “የጦር ወታደሮችህን ይዘህ ወደ ዐይ ከተማ ለመዝመት ውጣ፤ ከቶ አትፍራ፤ ደፋር ሁን፤ እኔ በዐይ ንጉሥ ላይ ድልን እንድትቀዳጅ አድርጌሃለሁ፤ ሕዝቡ፥ ከተማይቱና ምድሪቱ የአንተ ይሆናሉ፤

2 ከዚህ በፊት በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ የደረሰውን ጥፋት በዐይና በንጉሥዋም ላይ ደግሞ ትፈጽምባቸዋለህ፤ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከእርስዋ የሚገኘውን የንብረትና የከብት ምርኮ ለራሳችሁ ታደርጋላችሁ፤ ከኋላ በኩል በከተማይቱ ላይ በድንገት አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ።”

3 ስለዚህም፥ ኢያሱ ከወታደሮቹ ጋር በዐይ ላይ ዘመተ፤ ከሠራዊቱም የተሻለ ችሎታ ያላቸውን ሠላሳ ሺህ ወታደሮች መርጦ በሌሊት ሲልካቸው

4 እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው፦ “ከከተማይቱ በስተኋላ አድፍጣችሁ ቈዩ፤ ይሁን እንጂ ከከተማይቱ ብዙ ሳትርቁ አደጋ ለመጣል በሚያስችላችሁ ሁኔታ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፤

5 እኔና ከእኔ ጋር የተመደቡት የጦር ሰልፈኞች ወደ ከተማይቱ እንቀርባለን፤ የዐይ ወታደሮች በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል በሚመጡብን ጊዜ ልክ ከዚህ በፊት ባደረግነው ዐይነት ወደ ኋላ እንሸሻለን፤

6 ከእነርሱ እየሸሸን ሳለን እንደ ቀድሞው ከእኛ እየሸሹ ነው ይላሉ፤ ከከተማው እስክናርቃቸው ድረስ እኛን ይከተላሉ፤

7 በዚህን ጊዜ እናንተ ከተደበቃችሁበት ስፍራ ወጥታችሁ ከተማይቱን ያዙ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔርም ከተማይቱን ለእናንተ አሳልፎ ይሰጣችኋል።

8 ከተማይቱን ከያዛችሁ በኋላ፥ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእሳት አቃጥሉአት። እነሆ፥ አዝዤአችኋለሁ።”

9 ከዚህ በኋላ ኢያሱ ወታደሮቹን ላከ፤ ከዐይ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል ድብቅ ጦር ሆነው ቈዩ፤ ኢያሱም በሠራዊቱ መካከል ዐደረ።

10 በማግስቱም ጠዋት ኢያሱ ቀደም ብሎ በመነሣት ሕዝቡን ጠራ፤ እርሱና የእስራኤል መሪዎች ሁሉ ዘማቹን ጦር ወደ ዐይ መምራት ጀመሩ፤

11 ከእርሱም ጋር የነበረው ሠራዊት ወደ ፊት ቀድሞ በመጓዝ ወደ ከተማይቱ ቀረበ፤ በስተሰሜንም በኩል በእርሱና በዐይ መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈረ።

12 ኢያሱ አምስት ሺህ ሰዎችን ያኽል መርጦ ከከተማይቱ በስተምዕራብ በኩል በዐይና በቤትኤል መካከል እንዲሸምቁ አድርጎ ነበር።

13 እነርሱም ዋናውን ሠራዊት ከከተማ በስተሰሜን በኩል፥ የኋላውን ደጀን በስተምዕራብ በኩል አሰለፉ፤ ኢያሱ ግን ሌሊቱን በሸለቆው አሳለፈ።

14 የዐይ ንጉሥ ይህን በአየ ጊዜ እርሱና የከተማው ሕዝብ እስራኤልን በጦርነት ለመግጠም ወደ ዓራባ ፊት ለፊት ወጡ። ከከተማው በስተጀርባ በኩል የደጀን ጦር መኖሩን አላወቁም ነበር።

15 ኢያሱና ሠራዊቱ ሁሉ የተሸነፉ በማስመሰል ወደ ኋላ በማፈግፈግ ወደ ምድረ በዳ ሸሹ።

16 የከተማይቱም ሰዎች እርስ በርስ በመጠራራት በሙሉ ወጥተው እነርሱን ማሳደድ ቀጠሉ፤ ኢያሱንም በሚያሳድዱበት ጊዜ ከከተማይቱ እየራቁ ሄዱ።

17 በዐይ ወይም በቤትኤል የሚገኝ ሰው ሁሉ ወጥቶ እስራኤላውያንን ሲያሳድድ ከተማይቱ ባዶዋን ክፍት ሆና ቀረች።

18 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን፦ “ጦርህን በዐይ ከተማ ላይ አንሣ፤ እኔ እርስዋን ለአንተ አሳልፌ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢያሱም በእጁ ያለውን ጦር ወደ ከተማይቱ ዘረጋ።

19 እጁንም በዘረጋ ጊዜ ሸምቀው የነበሩት ወታደሮች ከቦታቸው ተነሥተው ወደፊት ሄዱ፤ ወደ ከተማዋም በፍጥነት ገብተው በቊጥጥራቸው ሥር አደረጓትና ወዲያውኑ አቃጠሉአት።

20 የዐይ ከተማ ሰዎችም ወደ ኋላ መለስ ብለው ባዩ ጊዜ የከተማይቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ የሸሹት እስራኤላውያን በአሳዳጆቻቸው ላይ ስለ ተመለሱባቸው፥ በየትም በኩል ለማምለጥ አልቻሉም።

21 ኢያሱና ከእርሱ ጋር ተሰልፎ የነበረው ሠራዊት ቀደም ብለው ያዘጋጁት ሽምቅ ጦር ከተማይቱን በቊጥጥር ሥር ማድረጉንና በእሳት ማቃጠሉን በተመለከቱ ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው የዐይን ሰዎች መቱ።

22 ወደ ከተማይቱም ገብተው የነበሩት እስራኤላውያን ወደ እነርሱ ወርደው የጦርነቱ ተካፋዮች ሆኑ፤ ስለዚህም የዐይን ሰዎች የተወሰኑ እስራኤላውያን በአንድ በኩል፥ ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል ከበዋቸው ስለ ነበረ ወደየትም ለማምለጥ አልቻሉም። ከእነርሱም አንድ እንኳ እንዳያመልጥ ወይም በሕይወት እንዳይኖር ሁሉንም ፈጁአቸው።

23 የዐይ ንጉሥ ግን ተማርኮ ወደ ኢያሱ ቀረበ።

24 እስራኤላውያን በሜዳና በምድረ በዳ ቀደም ሲል የዐይ ወታደሮች እነርሱን አሳደዋቸው በነበረው ስፍራ ሁሉንም ገድለው ከጨረሱ በኋላ ወደ ዐይ ከተማ ገብተው በዚያ የተረፉትንም በሰይፍ ፈጁአቸው።

25 በዚያን ቀን የሞቱት የዐይ ወንዶችና ሴቶች ዐሥራ ሁለት ሺህ ነበሩ።

26 ኢያሱም በዐይ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋባትን እጁን አላጠፈም።

27 እግዚአብሔርም ለኢያሱ በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በዚያች ያገኙትን የከብትና የሌላ ንብረት ምርኮ ሁሉ ለራሳቸው አደረጉ።

28 ኢያሱ የዐይን ከተማ በማቃጠል ለዘለዓለም ፍርስራሽ አድርጎ ተዋት፤ እስከ አሁንም ድረስ በዚህ ዐይነት ትገኛለች።

29 የዐይንም ከተማ ንጉሥ በእንጨት ላይ ሰቅሎ ሬሳው እስከ ማታ ተንጠልጥሎ እንዲቈይ አደረገ። ፀሐይም በምትጠልቅበት ጊዜ ሬሳው ከተሰቀለበት እንጨት ላይ ወርዶ በከተማይቱ ቅጽር በር መግቢያ እንዲጣል አደረገ፤ በእርሱም ላይ ብዙ የድንጋይ ቊልል ከመሩበት፤ የድንጋዩም ቊልል እስከ አሁን በዚያው ይገኛል።


ሙሴ የጻፈው ሕግ በዔባል ተራራ ላይ መነበቡ

30 ከዚህም በኋላ ኢያሱ በዔባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤

31 የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ እስራኤላውያንን ባዘዘው መሠረት በሙሴ አማካይነት በተሰጠው የሕግ መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጻፈው ባልተጠረበና ብረት ባልነካው ድንጋይ መሠዊያ ሠርተው የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድነት ቊርባን አቀረቡ።

32 ሙሴ ጽፎት የነበረውን የኦሪትን ሕግ ኢያሱ በእስራኤላውያን ፊት በድንጋይ ላይ ጻፈው።

33 የእስራኤልን ሕዝብ እንዲባርኩ ቀደም ብሎ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት እስራኤላውያን ሁሉና መጻተኞች ሽማግሌዎቻቸው፥ ሹሞቻቸውና ዳኞቻቸው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከተሸከሙት ከሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት ግራና ቀኝ እኩሌቶቹ ከጌሪዚም ተራራ ፊት ለፊት፥ እኩሌቶቹ ደግሞ ከኤባል ተራራ ፊት ለፊት ቆሙ።

34 ከዚህም በኋላ ኢያሱ በሕጉ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የሕጉን ቃላት በሙሉ በረከቱን፥ መርገሙንም ጭምር አነበበ።

35 ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሴቶች፥ በሕፃናትና በመጻተኞች ፊት ሙሴ ካዘዘው ሕግ አንዲት ቃል እንኳ ሳያስቀር አነበበ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች