ኢያሱ 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዓካን የፈጸመው በደል 1 እስራኤላውያን ግን የተከለከሉ ነገሮችን በተመለከተ ታማኞች ሆነው አልተገኙም፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ዓካን፥ የከርሚ ልጅ፥ የዘብዲ የልጅ ልጅ፥ የዛራ ልጅ ከተከለከሉት ነገሮች በመውሰድ በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቊጣ አስነሣ። 2 ኢያሱ በኢያሪኮ ሳለ በቤትአዌን አጠገብ ከቤትኤል በስተምሥራቅ የምትገኘውን “ዐይ” ተብላ የምትጠራውን ከተማና የምድሪቱን አቀማመጥ አጥንተው ይመለሱ ዘንድ ጥቂት ሰዎችን ላከ። ይህንንም በትእዛዙ መሠረት ከፈጸሙ በኋላ፥ 3 ለኢያሱ ከዚህ የሚከተለውን ማስረጃ አቀረቡለት፦ “እነርሱ ጥቂቶች ስለ ሆኑ በዐይ ላይ አደጋ ለመጣል ያለውን ሰው ሁሉ በአጠቃላይ ማዝመት አያስፈልግም፤ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ሰዎች ብቻ ላክ፤ በዚያ ለመዋጋት መላውን ሠራዊት አትላክ።” 4 ስለዚህም ሦስት ሺህ እስራኤላውያን ዘምተው አደጋ ጣሉባት፤ ነገር ግን እነርሱ ከዐይ ወታደሮች ፊት ሸሹ፤ 5 የዐይ ሰዎችም ወደ ሠላሳ ስድስት ያኽል ሰዎችን ገደሉባቸው፤ ከከተማይቱ ቅጥር በር ጀምሮ እስከ ሼባሪዎ ቊልቊለት ድረስ እየገደሉ አባረሩአቸው፤ የሕዝቡም ልብ ቀልጦ እንደ ውሃ ፈሰሰ። 6 ኢያሱና የእስራኤል መሪዎች በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ በእግዚአብሔርም ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግንባራቸው ተደፉ፤ ሐዘናቸውን ለመግለጥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ። 7 ኢያሱም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ወዮ! እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህን ሕዝብ ለምን ዮርዳኖስን አሻገርከው? አሞራውያን እንዲያጠፉን ለእነርሱ አሳልፈህ ለመስጠት ነውን? ከዮርዳኖስ ማዶ ብንቀመጥ እንዴት በተሻለን ነበር! 8 አምላክ ሆይ፥ እስራኤል ከጠላቶቹ ፊት ከሸሸ እንግዲህ ምን እላለሁ? 9 ከነዓናውያንና ሌሎችም በዚህች ምድር የሚኖሩት ሁሉ ይህን ነገር ይሰማሉ፤ ስለዚህም ዙሪያችንን ከበው ሁላችንንም ይፈጁናል፤ ታዲያ ስለ ክብርህ የምታደርገው ምንድን ነው?” 10 እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ! ስለምን በግንባርህ ወደቅኽ? 11 እስራኤላውያን በድለዋል፤ እንዲጠብቁት ያዘዝኳቸውንም ቃል ኪዳን አፍርሰዋል፤ ከተከለከሉት ነገሮች ወስደዋል፤ ሰርቀዋል፤ ከራሳቸው ንብረት ጋር በማቀላቀል አታላዮች ሆነዋል። 12 እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን መቋቋም ያልቻሉበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እነርሱ ራሳቸው እንዲጠፉ ስለ ተፈረደባቸው ከጠላቶች ፊት ወደ ኋላ ይሸሻሉ። እንዲደመሰስ የታዘዘውን ነገር ከመካከላችሁ ካላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋር አልሆንም። 13 ሂድ! ሕዝቡን አንጻ! ‘በመካከላችሁ የተከለከለ ነገር ስላለ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለነገ ራሳችሁን አንጹ!’ ይላል በላቸው። እስራኤል ሆይ! ይህን የተከለከለ ነገር ከመካከልህ ካላስወገድህ በጠላቶችህ ፊት ልትቆም አትችልም። 14 ስለዚህ ነገ ጧት በየነገዳችሁ ቅረቡ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ነገድ በየጐሣው ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ጐሣ በየቤተሰቡ ይቅረብ፤ እግዚአብሔር የሚለየው ቤተሰብ በየግለሰቡ ይቅረብ፤ 15 እርም የሆኑ (የተከለከሉ) ነገሮች የተገኙበትም ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስላፈረሰና በእስራኤል ላይ በደል ስለ ፈጸመ እርሱና የእርሱ የሆነ ሁሉ በእሳት ይቃጠል።” 16 በማግስቱም ማለዳ ኢያሱ እስራኤላውያንን በየነገዳቸው አምጥቶ አቀረባቸው፤ ከዚያም የይሁዳ ነገድ ለብቻው ተለየ፤ 17 ኢያሱም የይሁዳን ነገድ በየጐሣው አቀረበ፤ ከዚያም በኋላ የዛራሕ ጐሳ ለብቻው ተለየ፤ የዛራሕንም ጐሣ በየቤተሰቡ አቀረበው፤ የዛብዲም ቤተሰብ ለብቻው ተለየ፤ 18 የዛብዲንም ቤተሰብ በየግለሰቡ ለይቶ አቀረበ፤ በመጨረሻም የዛብዲ የልጅ ልጅ የሆነው የካርሚ ልጅ ዓካን ለብቻው ተለየ፤ 19 ኢያሱም ዓካንን “ልጄ ሆይ፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አክብር፤ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረግኸውንም ከእኔ ሳትደብቅ ንገረኝ” አለው። 20 ዓካንም እንዲህ ሲል መለሰ፥ “እውነት ነው፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የበደልኩ እኔ ነኝ፤ እነሆ፥ ያደረግኹትም ከዚህ የሚከተለው ነው፤ 21 ካገኘነው ዕቃ መካከል ውብ የሆነ የባቢሎናውያን ካባ፥ ሁለት ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብርና ግማሽ ኪሎ ያህል የሚመዝን ምዝምዝ ወርቅ አየሁ፤ እነርሱንም ለማግኘት ብርቱ ፍላጎት ስላደረብኝ ወስጃቸዋለሁ፤ እነርሱንም ብሩ ከታች ሆኖ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተቀብረዋል።” 22 ከዚህ በኋላ ኢያሱ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ወደ ድንኳኑ እየሮጡ ሄዱ፥ እዚያም ብር ከስር ሆኖ የተቀበሩት እርም የሆኑ ዕቃዎች ነበሩ፤ 23 እነርሱንም ከድንኳኑ በማውጣት፥ ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤላውያን አምጥተው በእግዚአብሔር ፊት አኖሩአቸው። 24 ኢያሱም ከመላው የእስራኤል ሕዝብ ጋር ዓካንን ይዞ ብሩን፥ ካባውን፥ የወርቅ ምዝምዙን ከዓካን ወንዶችና ሴቶች ልጆች ጋር ከብቶቹን፥ አህዮቹንና በጎቹን ጭምር፥ ድንኳኑንና የእርሱ ንብረት የሆነውን ሁሉ ሰብስቦ፥ ወደ አኮር ሸለቆ አመጣቸው፤ 25 ኢያሱም “ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ ያመጣህብን ስለምንድን ነው? እነሆ! በአንተም ላይ ዛሬ እግዚአብሔር መከራን ያመጣብሃል!” አለው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ዓካንን በድንጋይ ወግረው ገደሉት፤ ቤተሰቡንም በድንጋይ ወግረው ንብረቱን ሁሉ አቃጠሉ፤ 26 በእርሱም ላይ እስከ ዛሬ ድረስ የሚታይ ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት፤ እግዚአብሔርም ከቊጣው ተመለሰ፤ ስለዚህም ያ ቦታ የአኮር ሸለቆ ተብሎ ይጠራል። |