Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢያሱ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመታሰቢያ ድንጋዮች ስለ ማቆም የተሰጠ ትእዛዝ

1 የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፦

2 “ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሰው በመውሰድ ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ምረጥ፤

3 በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል፥ ካህናቱ ከቆሙበት ከዚያው ስፍራ ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይዘው እንዲወጡ እዘዛቸው፤ ድንጋዮቹንም ወስደው ዛሬ ማታ በምትሰፍሩበት ስፍራ ያቆሙአቸው ዘንድ ንገር።”

4 ኢያሱም የመረጣቸውን ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤

5 “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቀድማችሁ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ውረዱ፤ በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ስም፥ እያንዳንዳችሁ አንዳንድ ድንጋይ በማንሣት በትከሻችሁ ተሸከሙ።

6 እነዚህም ድንጋዮች እግዚአብሔር ያደረገውን ነገር ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ይሆናሉ፤ በሚመጡትም ዘመናት ልጆቻችሁ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድናቸው?’ ብለው በሚጠይቁአችሁ ጊዜ፥

7 እናንተም እንዲህ ብላችሁ ትነግሩአቸዋላችሁ፦ ‘የአምላካችሁ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚሻገርበት ጊዜ፥ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ መውረዱን አቆመ፤ ስለዚህም እነዚህ ድንጋዮች በዚህ ስፍራ የተደረገውን ሁሉ ለዘለቄታው ለእስራኤል ሕዝብ የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ናቸው።’ ”

8 ሰዎቹም ኢያሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔር ለኢያሱ በነገረው መሠረት በእስራኤል ነገዶች ቊጥር ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወደ ሰፈሩበት ቦታ ወስደው አስቀመጡ፤

9 ኢያሱም ደግሞ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸክመው በቆሙበት በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ዐሥራ ሁለት የመታሰቢያ ድንጋዮችን አቆሙ፤ እነዚያም ድንጋዮች እስከ ዛሬ በዚያው ይገኛሉ፤

10 ለሕዝቡ እንዲነግር እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት ሁሉ ነገር እስኪፈጸም ድረስ ካህናቱ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል እንደ ቆሙ ቈዩ፤ ሙሴም ኢያሱን ያዘዘው ይህንኑ ነበር፤ ሕዝቡም ፈጥኖ ወንዙን ተሻገሩ።

11 ሁሉም ተሻግረው ካበቁ በኋላ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት እንደገና ወደ ፊት ቀድመው ሕዝቡን መምራት ጀመሩ።

12 ከሮቤልና ከጋድ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ለጦርነት የተዘጋጁት ሰዎች ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት ከሕዝቡ ግንባር ቀደም ሆነው ተሻገሩ።

13 ከእነርሱም የተውጣጡ ብዛታቸው አርባ ሺህ ያኽል የሆነ ጦረኞች በእግዚአብሔር ፊት ተሰልፈው በኢያሪኮ አቅራቢያ ወደሚገኘው ሜዳ ተሻገሩ።

14 በዚያን ቀን እግዚአብሔር ኢያሱን በእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አደረገው፤ ሙሴን ያከብሩት እንደ ነበር ኢያሱንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ አከበሩት።

15 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፦

16 “የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ እዘዝ፤”

17 ኢያሱም ካህናቱን ከዮርዳኖስ ወንዝ እንዲወጡ አዘዘ።

18 የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙት ካህናት ከዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ወጥተው እግሮቻቸው ደረቁን መሬት በረገጡ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ ውሃ ወደ ቦታው ተመልሶ እንደ ቀድሞው ሞልቶ ይፈስ ጀመር።

19 ሕዝቡ የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን፥ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ከኢያሪኮ በስተምሥራቅ በኩል በሚገኘው በጌልገላ ሰፈሩ።

20 በጌልገላም ኢያሱ ከዮርዳኖስ ወንዝ የተወሰዱትን ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች አቁሞ፥

21 ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፦ “በሚመጡት ዘመናት የልጅ ልጆቻችሁ፦ ‘እነዚህ ድንጋዮች ምንድን ናቸው?’ ብለው ወላጆቻቸውን በሚጠይቁአቸው ጊዜ፦

22 የእስራኤል ሕዝብ የዮርዳኖስን ወንዝ በደረቅ ምድር የተሻገሩበት ጊዜ መኖሩን ትነግሩአቸዋላችሁ፤

23 አምላካችን እግዚአብሔር እስክንሻገር ድረስ አስቀድሞ ለእኛ የቀይ ባሕርን እንዳደረቀልን፥ ለእናንተም የዮርዳኖስን ወንዝ እስክትሻገሩ ድረስ ውሃ አድርቆ ያሻገራችሁ መሆኑን ንገሩአቸው፤

24 በዚህም ምክንያት በምድር ላይ የሚኖር ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔር ኀይል ምን ያኽል ታላቅ እንደ ሆነ ይገነዘባል፤ እናንተም አምላካችሁ እግዚአብሔርን ለዘለዓለም ታከብራላችሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች