Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዮናስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዮናስ ለእግዚአብሔር መታዘዝ

1 እግዚአብሔር ለሁለተኛ ጊዜ ዮናስን እንዲህ አለው፦

2 “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔም የምነግርህን ቃል ለሕዝቡ ዐውጅ።”

3 ዮናስም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሄደ፤ ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ ከመሆንዋ የተነሣ ከተማዋን በመላ ለማዳረስ ሦስት ቀን ይፈጅ ነበር።

4 ዮናስ ወደ ከተማይቱ ገብቶ ጒዞውን ጀመረ፤ የአንድ ቀን መንገድም እንደ ሄደ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች!” ብሎ ዐወጀ።

5 የነነዌ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል አመኑ፤ ጾምም ዐወጁ፤ መጸጸታቸውንም ለመግለጥ ከታላላቅ ጀምሮ እስከ ታናናሽ ድረስ ሁሉም ማቅ ለበሱ።

6 የነነዌ ንጉሥ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ፥ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሰ መንግሥቱንም በማውለቅ ማቅ ለብሶ ዐመድ ላይ ተቀመጠ።

7 ለነነዌም ሕዝብ እንዲህ ሲል ዐዋጅ አስነገረ፥ “ከንጉሡና ከመኳንንቱ በተላለፈው ትእዛዝ መሠረት፥ ማንም ሰው ወይም እንስሳ፥ የከብትም ሆነ የበግ መንጋ አንዳች ምግብ አይቅመሱ፤ ውሃም አይጠጡ፤

8 ሰዎችም ሆኑ እንስሶች ማቅ ይልበሱ፤ እያንዳንዱ ሰው ከልብ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ መጥፎ ጠባዩንና የግፍ ሥራውን ይተው።

9 እኛ ከጥፋት እንድንድን ምናልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ከሚያስፈራው ቊጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”

10 እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ያደረጉትንና ከክፉ መንገዳቸው መመለሳቸውን ተመለከተ፤ ስለዚህም ራርቶላቸው በእነርሱ ላይ ሊያመጣ የነበረውን ቅጣት አልፈጸመም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች