ዮሐንስ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “እነሆ፥ ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እምነታችሁ እንዳይናወጥ ብዬ ነው። 2 ከምኲራቦች አስወጥተው ያባርሩአችኋል፤ እንዲያውም እናንተን የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። 3 ይህንንም የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው። 4 ይህንን ለእናንተ መናገሬ ግን ጊዜው ሲደርስ ምን እንዳልኳችሁ እንድታስታውሱ ነው።” “ይህን ሁሉ ከአሁን በፊት ያልነገርኳችሁ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርኩ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ 5 አሁን ግን ወደ ላከኝ መሄዴ ነው፤ ሆኖም ከእናንተ ‘ወዴት ትሄዳለህ?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም። 6 ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ስለ ነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል። 7 እኔ ግን እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ መሄድ ለእናንተ ይጠቅማችኋል፤ እኔ ካልሄድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ከሄድኩ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ። 8 እርሱ በመጣ ጊዜ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድም ምክንያት የዓለምን ሰዎች ያጋልጣል። 9 ስለ ኃጢአት የሚያጋልጠው በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ 10 ስለ ጽድቅ የሚያጋልጠው ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ወዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ 11 ስለ ፍርድ የሚያጋልጠው የዚህ ዓለም ገዢ ስለ ተፈረደበት ነው። 12 “ገና የምነግራችሁ ብዙ ነገር አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ይከብዳችኋል፤ 13 የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ የሚናገረው የሰማውን እንጂ የራሱን ስላልሆነ እርሱ ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ይነግራችኋል። 14 የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሚነግራችሁ እኔን ያከብረኛል። 15 የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ ይነግራችኋል’ ያልኳችሁ ስለዚህ ነው። የሐዘናችሁ ወደ ደስታ መለወጥ 16 “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ እንደገናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ።” 17 ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶች፥ “ይህ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ፤ ደግሞ ወደ አብ እሄዳለሁ’ የሚለን ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። 18 “እንግዲህ ይህ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ የሚለው ነገር ምንድን ነው? የሚናገረውን ነገር አናውቅም” በመባባል መላልሰው ተጠያየቁ። 19 ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ የምትጠያየቁ፥ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ደግሞም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ታዩኛላችሁ’ ስላልኳችሁ ነውን? 20 እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻላችሁም፤ ዓለም ግን ደስ ይለዋል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል። 21 ሴት በምትወልድበት ጊዜ የምጥ ቀንዋ ስለ ደረሰ ታዝናለች፤ ከወለደች በኋላ ግን በዓለም ላይ ሕፃን ስለ ተወለደ ከመደሰትዋ የተነሣ ጭንቀትዋን አታስታውሰውም። 22 እንዲሁም እናንተ አሁን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን እኔ እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም። 23 “በዚያን ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ አብን በስሜ ብትለምኑት ሁሉን ነገር ይሰጣችኋል። 24 እስከ አሁን በስሜ ምንም ነገር አለመናችሁም፤ ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ደስታችሁም ፍጹም ይሆናል። 25 “እስከ አሁን በምሳሌ ነገርኳችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በምሳሌ የማልናገርበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ስለ አብ ሁሉን ነገር ገልጬ እነግራችኋለሁ። 26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ‘አብን እለምንላችኋለሁ’ አልላችሁም። 27 ምክንያቱም አብ ራሱ ስለሚወዳችሁ ነው፤ አብም የሚወዳችሁ እኔን ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣሁ ስላመናችሁ ነው። 28 ከአብ ዘንድ ወጥቼ፥ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ እንደገናም ይህን ዓለም ትቼ፥ ወደ አብ እሄዳለሁ።” 29 ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፤ “እነሆ! አሁን በምሳሌ ሳይሆን በግልጥ ተናገርክ፤ 30 አንተ ሁሉን እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ ሊያቀርብልህ እንደማያስፈልግህ አሁን ዐወቅን፤ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ወጣህ እናምናለን።” 31 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁንስ አምናችኋል? 32 ይሁን እንጂ እያንዳንዳችሁ በየበኩላችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፤ ሰዓቱም አሁን ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም። 33 ይህን ለእናንተ መናገሬ በእኔ ሆናችሁ ሰላም እንዲኖራችሁ ብዬ ነው፤ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” |