ዮሐንስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ 1 እነሆ፥ ጊዜው ከአይሁድ ፋሲካ በዓል በፊት ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን ዐወቀ። በዚህ በዓለም ያሉትን የራሱን ወገኖች ወዶአቸው ነበር፤ እስከ መጨረሻም ወደዳቸው። 2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ራት ይበሉ ነበር፤ የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ በልቡ ክፉ ሐሳብ አሳደረበት። 3 አብ ሥልጣንን ሁሉ እንደ ሰጠውና ከእግዚአብሔር ወጥቶ እንደመጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። 4 ስለዚህ ከማእድ ተነሣና ልብሱን አስቀመጠ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። 5 ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ዕቃ ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ፤ በታጠቀውም ማበሻ ጨርቅ እግራቸውን አበሰ። 6 ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። 7 ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። 8 ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። 9 ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። 10 ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። 11 ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። 12 እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? 13 እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። 14 እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። 15 እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። 16 እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። 17 ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ። 18 ይህን የምናገረው ስለ ሁላችሁም አይደለም፤ እኔ የመረጥኳችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ‘እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሣብኝ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም አለበት። 19 ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፤ ከተፈጸመ በኋላ፥ በእኔ ማንነት እንድታምኑ ነው። 20 እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ኢየሱስ አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ አስቀድሞ መናገሩ ( ማቴ. 26፥20-25 ፤ ማር. 14፥17-21 ፤ ሉቃ. 22፥21-23 ) 21 ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በመንፈሱ ተጨነቀና “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ገልጦ ተናገረ። 22 ደቀ መዛሙርቱ ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ባለማወቃቸው እርስ በእርሳቸው ተያዩ። 23 ኢየሱስ ይወደው የነበረው፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ጐን ተቀምጦ ነበር። 24 ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቀሰና “ስለ ማን እንደ ተናገረ እስቲ ጠይቅ” አለው። 25 ስለዚህ እርሱ አንገቱን ወደ ኢየሱስ አስጠጋና “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። 26 ኢየሱስም “እርሱ ይህን እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የማጐርሰው ነው” አለ። ይህንንም ብሎ እንጀራ በወጥ አጠቀሰና የአስቆሮታዊው ስምዖን ልጅ ለሆነው ለይሁዳ አጐረሰው። 27 ይሁዳ ጉርሻውን ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ሰይጣን ዐደረበት፤ ኢየሱስም ይሁዳን፥ “ለማድረግ ያሰብከውን ቶሎ ብለህ አድርግ!” አለው። 28 ኢየሱስ ስለምን ይህን እንዳለ በማእድ ከተቀመጡት ማንም የገባው የለም። 29 ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ ወይም ለድኾች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበር። 30 ይሁዳም ጉርሻውን እንደ ተቀበለ ወዲያውኑ ወጥቶ ሄደ፤ ጊዜውም ሌሊት ነበረ። አዲሱ ትእዛዝ 31 ይሁዳ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሮአል፤ በእርሱም አማካይነት እግዚአብሔር ከብሮአል፤ 32 እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፤ ሳይዘገይም ያከብረዋል። 33 ልጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ አልቆይም፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው፥ አሁንም ለእናንተ እንዲሁ እላችኋለሁ። 34 እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ። 35 እርስ በእርሳችሁ ከተዋደዳችሁ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል።” ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ መናገሩ ( ማቴ. 26፥31-35 ፤ ማር. 14፥27-31 ፤ ሉቃ. 22፥31-34 ) 36 ከዚህ በኋላ ስምዖን ጴጥሮስ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! ወዴት ነው የምትሄደው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰለት። 37 ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ስለምን አሁን ልከተልህ አልችልም? እኔ ሕይወቴን እንኳ ስለ አንተ አሳልፌ እሰጣለሁ” አለው። 38 ኢየሱስም “አንተ ሕይወትህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት፥ እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ዶሮ ከመጮሁ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ሲል መለሰ። |