Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኤርምያስ 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኤርምያስ መሬት መግዛቱ

1 የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥረኛው ዓመት፥ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት እግዚአብሔር እኔን ኤርምያስን ተናገረኝ፤

2 ያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊት በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል ከበባ ያደረገበት ጊዜ ነበር፤ እኔም በዚያን ጊዜ በቤተ መንግሥቱ ግቢ በሚገኘው በዘብ ጠባቂዎች ክፍል ውስጥ ተዘግቶብኝ ነበር፤

3 ንጉሥ ሴዴቅያስ እኔን በዚያ እስረኛ አድርጎ ያስቀመጠኝና የከሰሰኝ እግዚአብሔር የተናገረኝን የትንቢት ቃል ለእርሱ በማሳወቄ ሲሆን፥ እርሱም እንዲህ የሚል ነበር፥ “የባቢሎን ንጉሥ ይህችን ከተማ በኀይል እንዲይዝ ልፈቅድለት ነው፤

4 ንጉሥ ሴዴቅያስም ማምለጫ የለውም፤ እርሱ ለባቢሎን ንጉሥ ተላልፎ ይሰጣል፤ ንጉሡን ፊት ለፊት ያየዋል፤ በግሉም ያነጋግረዋል።

5 ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ይወሰዳል፤ እኔ በሞት እስክጐበኘው ድረስ በዚያ ይኖራል፤ ከባቢሎናውያን ጋር ለመዋጋት ቢሞክር እንኳ አይሳካለትም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

6 እንደገናም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

7 “አጐትህ የሻሉም ልጅ ሐናምኤል በብንያም ክፍል በዐናቶት የሚገኘውን መሬቱን እንድትገዛው ለመጠየቅ ወደ አንተ ይመጣል፤ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ያን መሬት መግዛት የሚገባህ አንተ ነህ።”

8 እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ሐናምኤል ታስሬ ወዳለሁበት ወደ ዘብ ጠባቂዎች ክፍል መጥቶ “የመግዛት መብት ያንተ ስለ ሆነ መሬቴን ግዛ” አለኝ፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር እንደ ተናገረኝ ዐወቅሁ።

9 መሬቱንም ከሐናምኤል ለመግዛት ገንዘቡን መዘንኩለት፤ የዋጋውም ልክ ወደ ሁለት ኪሎ የሚመዝን ብር ሆነ።

10 የግዢውንም ውል ምስክሮች ባሉበት ፈርሜ አሸግሁት፤ ገንዘቡንም በሚዛን መዝኜ ሰጠሁት።

11 ከዚያም አጠቃሎ ይዞ የታተመውንና ያልታተመውን የሽያጩን ውል ሁለት ግልባጭ ወስጄ፥

12 የማሕሴያ የልጅ ልጅ ለሆነው ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ሰጠሁት፤ እነዚያን ግልባጮች የሰጠሁት በሐናምኤል፥ የሽያጩን ውል በፈረሙት ምስክሮችና በአደባባዩ ተቀምጠው በነበሩት ሰዎች ፊት ነው፤

13 በእነርሱም ሁሉ ፊት ባሮክን እንዲህ አልኩት፥

14 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘የታሸገውንና ግልጥ የሆነውን ሁለቱንም የሽያጭ ውል ወረቀት ወስደህ በሸክላ ዕቃ ውስጥ እንድታኖረውና ለብዙ ዘመን ተጠብቆ እንዲኖር አድርግ፤’

15 እንደገና በዚህች ምድር ቤቶችን፥ የእርሻ መሬቶችን፥ የወይን ተክል ቦታዎችን መግዛት የሚቻልበት ጊዜ ይመጣል ብሎአል።”


የኤርምያስ ጸሎት

16 የሽያጩን ውል ለኔርያ ልጅ ለባሮክ ከሰጠሁት በኋላ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦

17 “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! በታላቁ ሥልጣንህና ኀይልህ ሰማይና ምድርን ፈጥረሃል፤ ከቶም የሚሳንህ ነገር የለም፤

18 ለብዙ ሺህ ሕዝብ ዘለዓለማዊ ፍቅርህን አሳይተሃል፤ ይሁን እንጂ አባቶቻቸው በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ልጆቻቸውን ትቀጣለህ፤ አንተ ታላቅና ኀያል አምላክ ነህ፤ አንተ ሁሉን ቻይና ስምህም የሠራዊት ጌታ ነው፤

19 ዓላማህ ታላቅ ነው፤ ሥራህም ኀያል ነው፤ ሕዝቦች የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ታያለህ፤ ለእያንዳንዱም ሰው እንደአካሄዱና እንደየሥራው ዋጋውን ትከፍላለህ።

20 በቀድሞ ጊዜ በግብጽ ምድር ተአምራትንና አስደናቂ ነገሮችን አደረግህ፤ እስከ አሁንም ድረስ እነዚያን ድንቅ ሥራዎች በእስራኤል ሕዝብና በሌሎች ሰዎች መካከል ከማድረግ አልተቈጠብክም፤ ከዚህም የተነሣ በሁሉ ስፍራ ስምህ ገኗል።

21 በተአምራትና በአስደናቂ ሁኔታ፥ በኀይልህና በታላቅነትህ፥ እንዲሁም በአስፈሪ ግርማህ ሕዝብህን እስራኤልን ከግብጽ ምድር አወጣህ፥

22 ለቀድሞ አባቶቻቸውም በሰጠሃቸው ተስፋ መሠረት ይህችን ብልጽግና የሞላባት ለምለም ምድር አወረስካቸው።

23 ነገር ግን ወደዚህች ምድር መጥተው ከወረሱአት በኋላ ለቃልህ መታዘዝንና በአስተማርካቸው ሕግ ጸንተው መኖርን እምቢ አሉ፤ ያዘዝካቸውንም ነገር ሁሉ አልፈጸሙም፤ ከዚህም የተነሣ ይህን ሁሉ ጥፋት አመጣህባቸው።

24 “እነሆ ባቢሎናውያን ከተማይቱን ለመያዝ ዐፈር ቈልለው ዙሪያዋን በመክበብ ላይ ናቸው፤ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር ከተማይቱ በእነርሱ እጅ እንድትወድቅ ያደርጓታል፤ እነሆ አንተ የተናገርከው ሁሉ መድረሱን ታያለህ፤

25 ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ከተማይቱ በባቢሎናውያን ልትያዝ ተቃርባ ሳለ መሬቱን በምስክሮች ፊት እንድገዛ ያዘዝከኝ አንተ ነህ።”

26 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

27 “የሰው ዘር ሁሉ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከቶ ለእኔ የሚሳነኝ ነገር አለን?

28 ይህችን ከተማ ለባቢሎናውያንና ለንጉሣቸው ለናቡከደነፆር አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እርሱም ይይዛታል።

29 ይህችን ከተማ የከበቡ ባቢሎናውያን መጥተው ያቃጥሉአታል፤ እንደዚሁም እኔን ለማስቈጣት በጣራዎቻቸው ላይ ለባዓል ጣዖት ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትንና ለሌሎችም ጣዖቶች የመጠጥ መሥዋዕት ያቀርቡባቸው የነበሩትን ቤቶች ያቃጥላሉ።

30 የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከክፉ አድራጎት በስተቀር ምንም ያደረጉት መልካም ነገር የለም። በተለየም የእስራኤል ሕዝብ በእጃቸው በሠሩት ጣዖት እኔን ከማስቈጣት በቀር ምንም የሠሩት ነገር የለም።

31 ይህች ከተማ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝብዋ እጅግ ስላስቈጡኝ ከተማይቱን ለማጥፋት ወስኜአለሁ።

32 የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ፥ የእነርሱ ነገሥታት፥ ባለሥልጣኖቻቸው፥ የእነርሱ ካህናትና ነቢያት በሚያደርጉአቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ ቊጣዬን አነሣሥተዋል።

33 እነርሱ እኔን ትተው ሄደዋል፤ ዘወትር በመደጋገም ባስተምራቸውም አልሰሙኝም፤ ተግሣጼንም አልተቀበሉም፤

34 ይልቁንም የስሜ መጠሪያ እንዲሆን በተሠራው መቅደሴ አጸያፊ የሆኑ ጣዖቶቻቸውን በማቆም አርክሰውታል።

35 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ሞሌክ ለተባለው ጣዖት መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በሄኖም ሸለቆ ውስጥ ለበዓል ጣዖት መሠዊያ ሠርተዋል፤ እኔ ይህን እንዲያደርጉ አላዘዝኳቸውም የይሁዳንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ለመምራት ይህን ያደርጋሉ ብዬ አልጠበቅሁም ነበር።”


አስተማማኝ ተስፋ

36 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ኤርምያስ ሆይ! እነሆ ሕዝቡ ‘ይህችን ከተማ ጦርነት፥ ራብና ቸነፈር በባቢሎን ንጉሥ እጅ እንድትወድቅ ሊያደርጉአት ነው’ ይላሉ፤ እነሆ እኔ የምለውን ሌላ ነገር ደግሞ ስማ፤

37 እንደ እሳት በሚነደው ታላቅ ቊጣዬ የበተንኳቸውን ሕዝብ ከተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ እንደገና ወደዚህ ቦታ እሰበስባቸዋለሁ፤ በሰላም እንዲኖሩም አደርጋለሁ።

38 እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ፤

39 አንድ ዓላማ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ፤ ይኸውም ለእነርሱና ለልጆቻቸው ሁሉ መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ዘወትር ያከብሩኝ ዘንድ ነው።

40 ከእነርሱ ጋር የዘለዓለም ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መልካም ነገር ከማድረግም አላቋርጥም፤ በእውነት እንዲፈሩኝ አደርጋለሁ። ከዚያም በኋላ ፊታቸውን ከእኔ ወደ ሌላ አይመልሱም።

41 እኔም ለእነርሱ መልካም ነገር በማድረግ ደስ ይለኛል፤ እኔ በፈቃዴ በዚህች ምድር በእውነት እመሠርታቸዋለሁ።

42 “በሕዝቡ ላይ ይህን ሁሉ ጥፋት እንዳመጣሁባቸው ሁሉ እንዲሁም ቃል የገባሁላቸውን መልካም ነገር እሰጣቸዋለሁ፤

43 ‘ምድሪቱ ለባቢሎናውያን ስለ ተሰጠች ሰዎችም ሆኑ እንስሶች የማይኖሩባት ባድማ ትሆናለች’ ባላችኋት በዚህች ምድር የእርሻ መሬት መግዛትና መሸጥ እንደገና ይጀመራል።

44 ሕዝቡ መሬት ይገዛሉ፤ ውሎች ተፈርመው በምስክሮች ፊት ይታተማሉ፤ ይህም ሁሉ በብንያም ክፍል በኢየሩሳሌም ዙሪያ ባሉ መንደሮች፥ በይሁዳ ገጠር ከተሞች፥ በተራራማው አገር ከተሞች፥ በኮረብቶች ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ሁሉ ይፈጸማል። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ምድራቸው ተመልሰው ንብረታቸውን እንዲረከቡ አደርጋለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች