ኤርምያስ 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእስራኤል ሕዝብ ወደ አገራቸው መመለስ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ አምላክ የምሆንበትና እነርሱም ሕዝቤ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል፤ 2 እስራኤል ዕረፍትን ለማግኘት ወደ ፊት በመጣ ጊዜ ከጦርነት የተረፉት በምድረ በዳ የእኔን የእግዚአብሔርን ምሕረት ያገኛሉ። 3 እኔ ለእነርሱ ከሩቅ ተገለጥኩላቸው፤ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ እነሆ እናንተን ለዘለዓለም ወደድኳችሁ፤ ዘለዓለማዊ ቸርነቴም ለእናንተ የጸና ይሆናል። 4 ሕዝቤ እስራኤል ሆይ፥ እንደገና ትገነባላችሁ፤ ትገነቢአለሽም፥ እንደገና ከበሮ ትይዢአለሽ፤ ከሚደሰቱት ጋር አብረሽ በመውጣት ትጨፍሪአለሽ። 5 እንደገናም በሰማርያ ኰረብቶች ላይ ወይን ትተክዪአለሽ ፍሬውንም የደከሙበት ሰዎች ይበሉታል፤ 6 ጠባቂዎች በኤፍሬም ተራራ ላይ ሆነው ‘ኑ አምላካችን እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጽዮን እንሂድ’ የሚሉበት ጊዜ ይመጣል።” 7 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሕዝቦች ሁሉ ስለምትበልጥ ስለ እስራኤል በደስታ ዘምሩ፤ ‘እግዚአብሔር ሕዝቡን አድኖአል፤ በእስራኤል ምድር የቀሩትን ሁሉ ተቤዥቶአል’ እያላችሁ የምስጋና መዝሙር አቅርቡ።” 8 “እኔ ከሰሜን አመጣቸዋለሁ፤ ከምድር ዳርቻም እሰበስባቸዋለሁ፤ ዕውሮች፤ አንካሶች፥ ነፍሰጡሮችና በምጥ የተያዙ ሴቶች ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብረው ይመጣሉ፤ ታላቅ ሕዝብ ሆነው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፤ 9 እኔ ወደ አገራቸው ስመራቸው ሕዝቤ ከደስታ የተነሣ እያለቀሱና እየጸለዩ ይመለሳሉ። በማይሰናከሉበት የተስተካከለ መንገድ ወደ ጥሩ ውሃ ምንጭ እመራቸዋለሁ። እኔ ለእስራኤል አባት ነኝ፤ ኤፍሬምም የበኲር ልጄ ነው።” 10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቦች ሆይ! አድምጡኝ፤ በሩቅ ጠረፎችም ቃሌን ዐውጁ፤ እኔ ሕዝቤን በትኜ ነበር፤ አሁን ግን እሰበስባቸዋለሁ፤ እረኛ መንጋውን እንደሚጠብቅም እጠብቃቸዋለሁ። 11 እኔ የእስራኤልን ሕዝብ ነጻ አውጥቼአቸዋለሁ፤ ከኀያል መንግሥትም እጅ በመታደግ አድኛቸዋለሁ፤ 12 ስለዚህም ተመልሰው መጥተው በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በምሰጣቸውም የእህል፥ የወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ የበግና የቀንድ ከብት በረከት ሁሉ ተድላ ደስታ ያደርጋሉ፤ በቂ ውሃ እንዳገኘች የተክል ቦታ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲያም አያዝኑም። 13 ልጃገረዶቻቸውም በደስታ ይጨፍራሉ፤ ወንዶች ወጣቶችና ሽማግሌዎችም ደስ ይላቸዋል፤ አጽናናቸዋለሁ፤ ለቅሶአቸውን ወደ ደስታ፥ ሐዘናቸውንም ወደ ሐሴት እለውጣለሁ፤ 14 ካህናቱን በምድሪቱ በረከት አጠግባቸዋለሁ፤ ለሕዝቤም ቸርነቴን አትረፈርፍላቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” የእግዚአብሔር ምሕረት በእስራኤል ላይ 15 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዋይታና የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ ታለቅሳለች፤ ልጆችዋ በሕይወት ስለሌሉ መጽናናትን እምቢ አለች። 16 ለቅሶአችሁን አቁማችሁ እንባችሁን ጥረጉ፤ ስለ ልጆቻችሁ ያደረጋችኹት ነገር ሁሉ ያለ ዋጋ አይቀርም፤ እነርሱ ከጠላት አገር ተመልሰው ይመጣሉ። 17 ልጆቻችሁ ወደ አገራቸው ተመልሰው ስለሚመጡ፥ የወደፊት ተስፋ አላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 18 “የእስራኤል ሕዝብ በሐዘን እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፤ ‘እግዚአብሔር ሆይ! እኛ እንዳልተገራ ወይፈን ነበርን፤ አንተ ግን መታዘዝን አስተማርከን፤ አንተ አምላካችን ስለ ሆንክ አሁንም ወደ አንተ ወደ አምላካችን መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን። 19 ከአንተ ርቀን ብንሄድም እንኳ አሁን ንስሓ ገብተናል፤ በዕፍረትና በጸጸት ራሳችንን ዝቅ አድርገን ደረታችንን እንመታለን፤ በወጣትነት ዘመናችን ለፈጸምነው ኃጢአት ራሳችንን እንወቅሳለን።’ 20 “እስራኤል ሆይ! እናንተ የተወደዳችሁ ልጆቼ ናችሁ፤ ከሁሉ አስበልጬ የምወዳችሁ አይደለምን? ምሕረት አደርግላችሁ ዘንድ ወደ እኔ ላቀርባችሁ እፈቅዳለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 21 ለራሳችሁ የመንገድ ምልክቶችን አድርጉ፤ መንገድንም የሚመሩ ዐምዶችን ትከሉ፤ የሄዳችሁበትን ዐውራ ጐዳና አተኲራችሁ ተመልከቱ፤ ሕዝቤ እስራኤል ሆይ! ወደ እነዚህ ከተሞቻችሁ ተመለሱ። 22 እናንተ እምነት የጐደላችሁ ሕዝብ፥ እስከ መቼ ታመነታላችሁ? እኔ እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገርን ፈጥሬአለሁ፤ ይኸውም ሴት ለወንድ ትከላከላለች። ልዩ የሆነ አዲስ ነገር ፈጥሬአለሁ።” የእግዚአብሔር ሕዝብ የወደፊት ብልጽግና 23 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን ወደ አገራቸው በመለስኩ ጊዜ በይሁዳና በከተሞቹ እንደገና ‘አንቺ የእውነት ማደሪያ የሆንሽ ቅድስት ተራራ እግዚአብሔር ይባርክሽ’ ይላሉ። 24 ‘ይሁዳና ከተሞቹ ሁሉ የሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ምድርን የሚያርሱ ገበሬዎችና መንጋን የሚጠብቁ እረኞች በዚያ ይገኛሉ፤ 25 የደከሙትን ሁሉ ኀይላቸው እንዲታደስ አደርጋለሁ፤ በረሀብ ዝለው የነበሩትንም ምግብ በመስጠት አጠግባቸዋለሁ፤ 26 ስለዚህም በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ‘ተኝተን ስንነቃ ታደስን’ ይላሉ። 27 “እኔ እግዚአብሔር የእስራኤልንና የይሁዳን ምድር በሕዝብና በእንስሶች የምሞላበት ጊዜ ይመጣል። 28 እነርሱን ለመንቀልና ለማፍረስ፥ ለመገለባበጥና ለማጥፋት፥ ለመደምሰስም እከታተል የነበርኩትን ያኽል፥ እነርሱን እንደገና ለመትከልና ለማነጽም እከታተላለሁ። 29 በዚያ ዘመን፥ ‘አባቶች የበሉት ጎምዛዛ የሆነ የወይን ፍሬ፥ የልጆችን ጥርስ አጠረሰ’ እየተባለ የሚነገረው ምሳሌ ይቀራል። 30 ይህ መሆኑ ቀርቶ ጎምዛዛ የወይን ፍሬ የሚበላ ሰው ሁሉ የገዛ ራሱን ጥርስ ብቻ ያጠርሳል፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ኃጢአት ይሞታል።” 31 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብና ከይሁዳ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ጊዜ ይመጣል፤ 32 ይህም ቃል ኪዳን እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት እጃቸውን በያዝኩ ጊዜ እንደ ገባሁት ቃል ኪዳን ያለ አይደለም፤ እኔ አምላካቸው ብሆንም እንኳ እነርሱ ቃል ኪዳኔን አልጠበቁም፤ እኔም ችላ አልኳቸው፤ 33 እነሆ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ፤ 34 ከእንግዲህ ወዲህ ‘እግዚአብሔርን ዕወቅ’ ብሎ ባልንጀራውንም ሆነ ወንድሙን የሚያስተምር ማንም አይኖርም፤ ከትልቁ ጀምሮ እስከ ትንሹ ሁሉም ያውቁኛል፤ በደላቸውን ይቅር እልላቸዋለሁ፤ ኃጢአታቸውንም አላስታውስባቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” 35 ፀሐይን በቀን እንዲያበራ የሚያደርገው፥ ጨረቃና ከዋክብት በሌሊት እንዲያበሩ ሥርዓትን የወሰነላቸው፥ ባሕሩን በማዕበል እንዲናወጥ የሚቀሰቅሰው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ስሙም የሠራዊት አምላክ ነው። 36 የተፈጥሮ ሥርዓት ጸንቶ እስከ ኖረ ድረስ እስራኤል በፊቱ ሕዝብ ሆና የምትኖር መሆንዋን የሚገልጥ ተስፋ ይሰጣል፤ 37 እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በሠሩት በደል ምክንያት ይጥላቸዋል ማለት የሚቻለው የሰማይ ስፋቱ ተለክቶ፥ የምድርም መሠረቶች ሁሉ ተመርምረው ለመታወቅ ቢችሉ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። 38 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሐናንኤል መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ እስከ ማእዘኑ የቅጽር በር ድረስ ኢየሩሳሌም የእኔ ከተማ ሆና የምትታነጽበት ጊዜ ይመጣል። 39 የወሰኑም መስመር ከማእዘኑ ቅጥር በር ወደ ጋሬብ ኰረብታ ይሄድና ወደ ጎዓ ይዞራል። 40 በድንና ዐመድ የሚጣልበት መላው ሸለቆ በምሥራቅ በኩል እስከ ፈረስ በር ድረስ እንኳ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ከተማይቱም እንደገና ከቶ አትፈርስም፤ አትደመሰስምም።” |