ኤርምያስ 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሁለቱ የበለስ ፍሬ ቅርጫቶች ምሳሌ 1 እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት የተቀመጡ ሁለት የበለስ ፍሬ ቅርጫቶችን አሳየኝ፤ ይህም የሆነው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የኢዮአቄም ልጅ የሆነውን የይሁዳ ንጉሥ ኢኮንያንን ከይሁዳ መሪዎች፥ ከእጅ ጥበብ ባለሞያዎችና ከሌሎችም ብልኀተኞች ሠራተኞች ጋር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን አስሮ ከወሰደ በኋላ ነው። 2 የመጀመሪያው ቅርጫት ከሌሎቹ በፊት ቀደም ብለው የበሰሉ መልካም የበለስ ፍሬዎችን የያዘ ነው፤ ሁለተኛው ቅርጫት ደግሞ ለመብል የማይሆኑ የተበላሹ በለሶችን የያዘ ነው፤ 3 እግዚአብሔርም “ኤርምያስ ሆይ! ይህ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም “እነሆ የበለስ ፍሬዎችን አያለሁ፤ ጥሩዎቹ ፍሬዎች እጅግ የተዋቡ ናቸው፤ መጥፎዎቹ ፍሬዎች ደግሞ ለምግብነት ደስ የማይሉና እጅግ የተበላሹ ናቸው” ስል መለስኩለት። 4 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 5 “እኔ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ወደ ባቢሎን የላክኋቸውን ሕዝብ እንደነዚህ ጥሩ የበለስ ፍሬዎች እንደ ሆኑ እቈጥራለሁ፤ 6 ለሕይወታቸውም በመጠንቀቅ ወደዚህች ምድር እንዲመለሱ አደርጋለሁ፤ አንጻቸዋለሁ፤ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ፤ አልነቅላቸውም፤ 7 እኔ እግዚአብሔር መሆኔን እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ። ከዚያ በኋላም በሙሉ ልባቸው ወደ እኔ ስለሚመለሱ፥ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ። 8 “የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስንና በዙሪያው ያሉትን አማካሪዎቹን፥ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በዚህች ምድር የተረፉትንና ወደ ግብጽ የወረዱትን ሁሉ ግን ለምግብነት ደስ እንደማያሰኙና እጅግ እንደተበላሹት እንደእነዚያ የበለስ ፍሬዎች አደርጋቸዋለሁ። 9 በስደት እንዲበታተኑ ባደረግሁባቸው በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ የተጠሉ፥ የተሰደቡ፥ የመነጋገሪያ ርእስ የሆኑ፥ መሳለቂያና የተወገዙ እንዲሆኑ አደርጋቸዋለሁ። 10 ለእነርሱና ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጠኋት ከዚህች ምድር እስኪጠፉ ድረስ በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር እንዲያልቁ አደርጋለሁ።” |