Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ኢሳይያስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዘለዓለማዊ ሰላም
( ሚክ. 4፥1-3 )

1 የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳ አገርና ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦

2 የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተሠራበት ተራራ ከሌሎች ተራራዎች ሁሉ በልጦ ይታያል፤ ከኰረብቶችም ሁሉ እጅግ ከፍ ይላል፤ የብዙ መንግሥታት ሕዝቦች ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።

3 ስለዚህ ብዙ ሕዝቦች እንዲህ ይላሉ፦ “ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ስለሚገኝ ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ እንውጣ፤ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤተ መቅደስም እንሂድ፤ እርሱ ፈቃዱን እንድናደርግ ያስተምረናል፤ እኛም በእርሱ መንገድ እንሄዳለን።”

4 እርሱ በብዙ መንግሥታት መካከል በመፍረድ አለመግባባትን ያስወግዳል፤ ስለዚህም ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውንም ወደ ማጭድ ይለውጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ጦርነት አያነሣም፤ ከዚያም በኋላ የጦር ትምህርት የሚማር አይኖርም።

5 እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ! ኑ! በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ!


የእልኸኛነት መወገድ

6 አምላክ ሆይ! የያዕቆብ ዘሮች የሆኑ ሕዝብህን እርግፍ አድርገህ ትተሃል፤ ምድሪቱ በምሥራቅ አገር ሰዎች ጥንቈላና በፍልስጥኤማውያን ሟርት ተሞልታለች፤ ሕዝቡም ከአሕዛብ ጋር ተባብረዋል።

7 ምድራቸው በብርና በወርቅ ስለ ተሞላች፥ ሀብታቸው ከመጠን በላይ ነው፤ አገራቸው በፈረሶች የተሞላች ሆናለች፤ ሠረገሎቻቸውም እጅግ ብዙ ናቸው።

8 ከዚህም ጋር ምድራቸው በጣዖት የተሞላች ሆናለች፤ በገዛ እጃቸውም ለሠሩት ምስል ይሰግዳሉ።

9 ከዚህም የተነሣ በሁሉም ላይ ኀፍረትና ውርደት ይደርስባቸዋል፤ ጌታ ሆይ! በደላቸውን ይቅር አትበል!

10 ከእግዚአብሔር ቊጣና ከአስፈሪ ግርማው ለማምለጥ በአለት ስንጣቂ ዋሻና በመሬት ጒድጓድ ውስጥ ተሸሸጉ!

11 ትዕቢተኞች ይዋረዳሉ፤ ኩራተኞችም ይቀላሉ፤ እግዚአብሔር ብቻ በክብር ከፍ ከፍ ይላል፤

12 የሠራዊት አምላክ ትዕቢተኞችና ኩራተኞች የሚዋረዱበትን ቀን ወስኖአል።

13 እርሱ ታላላቅ የሊባኖስ ዛፎችንና የባሳን የወርካ ዛፎችን ያጠፋል።

14 ታላላቅ ተራራዎችንና ኰረብቶችን ዝቅ በማድረግ ደልዳላ ቦታ ያደርጋቸዋል።

15 ረጃጅም የከተማ መጠበቂያ ግንቦችንና የጦር ምሽጎችን ሁሉ ዝቅ ያደርጋል፤

16 እጅግ የተዋቡ ዕቃዎችንና የተርሴስ መርከቦችን እንኳ ያሰጥማል፤

17-18 የሰዎች ኲራት ይጠፋል፤ እብሪት የሞላበት ትዕቢታቸውም ያከትማል፤ ጣዖቶች ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ብቻ በክብር ከፍ ከፍ ይላል።

19 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚመጣበት ጊዜ ከቊጣውና ከአስፈሪ ግርማው ለማምለጥ በአለት ዋሻና በመሬት ንቃቃት ውስጥ ለመሸሸግ ይሞክራሉ።

20 ሰዎች ይሰግዱላቸው ዘንድ በእጃቸው የሠሩአቸውን የብርና የወርቅ ምስሎች ለፍልፈሎችና ለሌሊት ወፎች እየጣሉላቸው ይሄዳሉ።

21 እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚመጣበት ጊዜ ከቊጣውና ከአስፈሪ ግርማው ተሰውረው ለማምለጥ በድንጋይ ዋሻና በተሰነጠቀ አለት ውስጥ ይሸሸጋሉ።

22 እንግዲህ ትንፋሹ አፍንጫው ላይ በሆነች በሟች ሰው መተማመናችሁ ይቅር፤ እርሱ ለምንም አይጠቅምም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች