Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሆሴዕ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ስለዚህ ወንድሞቻችሁ የሆኑትን እስራኤላውያንን “አሚ” እኅቶቻችሁንም “ሩሃማ” ብላችሁ ጥሩአቸው።


የእስራኤል ሕዝብ ባለመታመኑ መቀጣቱ

2 ልጆቼ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ እናታችሁ ሚስቴ ስላልሆነችና እኔም ባልዋ ስላልሆንኩ የዝሙት አመለካከትዋንና አመንዝራነትዋን እንድታስወግድ ውቀስዋት።

3 ባትመለስ ግን እንደ ተወለደችበት ቀን እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ እንደ ደረቀ ባዶ ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ።

4 ከዘማዊት ሴት የተወለዱ ስለ ሆኑ ለልጆችዋም አልራራላቸውም።

5 እናታቸው አመንዝራ ስለ ሆነች እነርሱን ባሳፋሪ መንገድ ፀንሳቸዋለች፤ እርስዋም ይህን ያደረገችው ምግቤንና ውሃዬን፥ የሱፍና የተልባ እግር ልብሴን፥ ዘይቴንና መጠጤን የሚሰጡኝ ስለ ሆነ ፍቅረኞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ ብላ ነው።

6 ስለዚህ መንገድዋን በእሾኽ እዘጋዋለሁ፤ መውጫ በር እንዳታገኝም ዙሪያውን በግንብ አጥራለሁ።

7 ፍቅረኞችዋን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን ልትደርስባቸው አትችልም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ ከዚህ በኋላ “ከአሁኑ ኑሮዬ ይልቅ የዱሮው ይሻለኛል፤ ስለዚህ ወደ ቀድሞው ባሌ እሄዳለሁ” ትላለች።

8 እርስዋ እህልን፥ የወይን ጠጅን፥ የወይራ ዘይትን የሰጠኋት፥ እኔ እንደ ሆንኩ ከቶ አልተገነዘበችም፤ እኔ ያበዛሁላትን ብርና ወርቅ “በዓል” ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት አቀረበች።

9 እህሉን በመከር ጊዜ ወይኑንም በወቅቱ እወስድባታለሁ፤ ራቁትነትዋን የምትሸፍንባቸውን የሱፍና የተልባ እግር ልብሶቼንም እወስድባታለሁ።

10 በፍቅረኞችዋም ፊት እርቃንዋን አስቀራታለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም።

11 የምትደሰትባቸውን በዓላትዋን ሁሉ ሰንበትዋን፥ ዓመታዊና ወርኀዊ በዓላትዋን እሽራለሁ፤ የተለዩ በዓላትዋንም ሁሉ እንዳታከብር አደርጋታለሁ።

12 ከፍቅረኛዎችዋም ያገኘቻቸውን የወይን ተክሎችና የበለስ ዛፎች እነቃቅላለሁ፤ የወይንና የፍራፍሬ እርሻዎችዋን ወደ ጫካነት እለውጣለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉአቸዋል።

13 “በዓል” ለሚባለው ጣዖት ለማጠንና ጌጣጌጥዋን አድርጋ ፍቅረኛዎችዋን በመከተል እኔን በመተዋ እቀጣታለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።


እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር

14 ስለዚህ እንደገና ወደ በረሓ እወስዳታለሁ፤ እዚያም በፍቅር ቃል አባብዬ እማርካታለሁ።

15 የቀድሞውን የወይን ተክል እመልስላታለሁ፤ የመከራንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ፤ እዚያም ከግብጽ ስትወጣ በወጣትነትዋ ወራት በነበራት ሁኔታ በደስታ ትዘምራለች።

16 በዚያን ቀን “ባለቤቴ” ብላ እንጂ እንደ በዓል ጣዖት “ጌታዬ” ብላ አትጠራኝም።

17 ከአንደበትዋ የ“በዓል” ጣዖቶችን ስም ለማስወግድ የእነርሱ ስም ዳግመኛ አይጠራም።

18 በዚያን ጊዜ ስለ እናንተ ከአራዊት፥ ከሰማይ ወፎችና በደረታቸው በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረቶች ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከምድሪቱም ላይ ቀስትን፥ ሰይፍንና ጦርነትን አስወግዳለሁ፤ እናንተንም በሰላም እንድታርፉ አደርጋለሁ።

19 እስራኤል ሆይ! ለዘለዓለም እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤ በጽድቅ፥ በፍትሕ፥ በዘለዓለማዊ ፍቅርና በምሕረት እንደ ባለቤቴ እንድትሆኚ አደርጋለሁ።

20 ቃል ኪዳኔን በመጠበቅ እንደ ባለቤቴ አደርግሻለሁ፤ አንቺም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቂያለሽ።

21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን እኔ መልስ አሰጣለሁ፤ እኔ ለሰማያት መልስ እሰጣለሁ፤ ሰማያትም ለምድር መልስ ይሰጣሉ።

22 ምድርም እህልን፥ ወይንንና የወይራ ዘይትን በማስገኘት ለኢይዝራኤል መልስ ትሰጣለች።

23 ሕዝቤን በምድሪቱ ላይ እመሠርታለሁ፤ እንዲበለጽጉም አደርጋቸዋለሁ፤ ‘ምሕረት አይደረግላችሁም’ የተባሉትን ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ የተባሉትንም ‘ሕዝቤ ናችሁ’ እላቸዋለሁ፤ እነርሱም ‘አንተ አምላካችን ነህ’ ይሉኛል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች