Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መክብብ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ራስ ወዳድነት ዋጋቢስ መሆኑ

1 ራሴን ለማስደሰትና የደስታንም ትርጒም መርምሬ ለማወቅ ወሰንኩ፤ ነገር ግን ይህም ከንቱ ሆኖ አገኘሁት።

2 ሳቅ ከሞኝነት ያልተሻለ፥ ተድላ ደስታም ዋጋ የሌለው ነገር መሆኑን አስተዋልኩ።

3 ይህም ሁሉ ሆኖ ጥበብን ለማግኘት ባለኝ ምኞት በመመራት ልቤን በወይን ጠጅ እያስደሰትኩ የምዝናናበት ጊዜ እንዲኖረኝ ለማድረግ በሞኝነት ወሰንኩ፤ ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ በሚኖሩበት በአጭር ዕድሜአቸው ሊያገኙት የሚገባ የተሻለ መልካም ዕድል ይህ ብቻ መሆኑን አሰብኩ።

4 ደግሞም አንድ ትልቅ ነገር ፈጸምኩ፤ ይኸውም፥ መኖሪያ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይን ተከልኩ፤

5 የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች፥ የአበባና የአትክልት ቦታዎችን አዘጋጀሁ፤

6 የሚያድጉ ዛፎችን ለማጠጣት የውሃ ግድቦችን ሠራሁ፤

7 ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችን ገዛሁ፤ ሌሎች የቤት ውልድ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ብዙ የከብት፥ የፍየልና የበግ መንጋ አረባሁ።

8 እኔ በምገዛው አገር ሁሉ ከልዩ ልዩ አውራጃዎች የከበሩ የቤተ መንግሥት መዛግብትን በመሰብሰብ ብዙ ወርቅና ብር አከማቸሁ፤ እኔን የሚያሞግሡ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችንም አዘጋጀሁ፤ ለሰው ተድላና ደስታን ሊሰጡ የሚችሉ እጅግ ብዙ ሴቶችንም ሰበሰብኩ።

9 ከዚህም የተነሣ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ የከበርኩ ታላቅ ሰው ሆንኩ፤ ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸንታ ኖረች።

10 ዐይኔ ያየውንና ልቤ የተመኘውን ሁሉ አገኘሁ፤ ለሰውነቴም የሚያስፈልገውን ደስታ ሁሉ አልነፈግሁትም፤ ደክሜ በሠራሁት ነገር ሁሉ ስለምደሰትበት እንግዲህ የእኔ ዕድል ፈንታ ይህ ነበር።

11 ይህን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ ያንን የሠራሁትን ነገር ሁሉ ምን ያኽል እንደ ደከምኩበት ስመለከት ከቊጥር የማይገባ ዋጋቢስ መሆኑን ተረዳሁ፤ እንዲያውም ምንም የማይጠቅምና ነፋስን እንደ መጨበጥ የሚያስቈጥር ሆኖ አገኘሁት።

12 መቼም ንጉሥ መሥራት የሚችለው ከእርሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት የሠሩትን በመከተል ነው፤ ስለዚህ እኔም ጥበብ፥ ሞኝነትና እብደት ምን እንደ ሆኑ መርምሬ ለማወቅ ማሰብ ጀመርኩ።

13 እንዲህም አልኩ “በእርግጥ ብርሃን ከጨለማ እንደሚሻል ጥበብም ከሞኝነት መሻልዋን ተመለከትኩ።

14 ጥበበኞች ሰዎች መነሻና መድረሻቸውን ያውቃሉ፤ ሞኞች ግን ይህን ሁሉ አያውቁም፤” ይሁን እንጂ ጥበበኛም ሆነ ሞኝ ሁለቱም የሚኖራቸው ዕድል አንድ ዐይነት መሆኑን ተረዳሁ።

15 ስለዚህም “ለሞኝ የሚደርሰው ዕድል ለእኔም ይደርሳል፤ ታዲያ፥ ይህን ያኽል ጥበበኛ የመሆኔ ትርፉ ምንድን ነው?” ብዬ በልቤ አሰብኩ። ወዲያውኑ “ይህ ሁሉ ከንቱ ነው!” አልኩ።

16 ጥበበኛንም ሆነ ሞኝን ሁለቱንም ለረጅም ጊዜ የሚያስታውሳቸው አይገኝም፤ በሚመጣው ዘመን ሁላችንም የተረሳን ሆነን እንቀራለን፤ ጥበበኞችም ሆንን ሞኞች፥ ሁላችንንም ሞት ይጠብቀናል።

17 ከመከራ በቀር ያገኘሁባት ጥቅም ባለመኖሩ ሕይወት በእኔ ዘንድ ትርጒም አልተገኘላትም፤ ይህም ከንቱ ስለ ነበር ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ይቈጠራል።

18 ያለኝን ሀብት ሁሉ ከእኔ በኋላ ለሚተካው ትቼለት ስለምሄድ በዚህ ዓለም የደከምኩበትና ያተረፍኩት ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፤

19 ከእኔ በኋላ የሚመጣው ጠቢብ ይሁን ሞኝ ተለይቶ አይታወቅም፤ ይሁን እንጂ እኔ የደከምኩበትንና በጥበቤ ያተረፍኩትን ነገር ሁሉ ወስዶ ባለቤት ይሆናል፤ ይህም ከንቱ ነው።

20 ስለዚህ በዚህ ዓለም የሠራሁትንና የደከምኩበትን ነገር ሁሉ ሳስታውስ ተስፋ አስቈረጠኝ።

21 ባለህ ጥበብ፥ በቀሰምከውም ዕውቀትና ብልኀት የለፋህበትን ሁሉ ምንም ላልደከመበት ሰው ትተህለት ታልፋለህ፤ ይህም ከንቱ ስለ ሆነ ታላቅ መከራ ነው።

22 ታዲያ፥ አስቦና ተጨንቆ በሕይወት ዘመኑ በሚደክምበት ነገር ሁሉ ሰው የሚያተርፈው ቁም ነገር ምንድን ነው?

23 በሕይወቱ ዘመን የሚሠራው ነገር ሁሉ ከሐዘንና ከትካዜ በቀር የሚያተርፍለት ምንም ዐይነት ጥቅም የለም፤ ሌሊት እንኳ አእምሮው ዕረፍት አያገኝም፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው።

24 እንግዲህ ለሰው የሚጠቅመው ነገር ቢኖር፥ ደክሞ በመሥራት ያፈራውን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት ራሱን ለማስደሰት መቻሉ ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠ መሆኑን ተረድቼአለሁ።

25 ያለ እርሱ ፈቃድማ እየበላና እየጠጣ ተድላ ደስታ ማድረግ የሚችል ማን አለ?

26 እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኘው ሰው ብቻ ጥበብን፥ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ሰው ግን ድካምን ብቻ ያተርፍለታል፤ ስለዚህም እርሱ ያከማቸውን ሀብት ሁሉ ምንም ላልደከመበት እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኝ ለሌላ ሰው ትቶለት እንዲያልፍ ያደርገዋል፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች