Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘዳግም 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ታላቁ ትእዛዝ

1 “አሁን ተሻግራችሁ በርስትነት በሚሰጣችሁ ምድር እንድትጠብቁት እግዚአብሔር አምላክህ እንዳስተምርህ ያዘዘኝ ትእዛዞች፥ ሕግና ሥርዓት እነዚህ ናቸው።

2 በዚያች ምድር ለረጅም ዘመናት መኖር እንድትችሉ አንተና ልጆችህ፥ የልጅ ልጆችህም በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን መፍራትና እኔ ለሰጠኋችሁ ደንቦችና ትእዛዞች ታዛዦች መሆን ይገባችኋል።

3 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነዚህን ሕግጋት አድምጡ! ታዘዙላቸውም! ይህን ብታደርጉ ለቀድሞ አባቶቻችሁ እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በማርና በወተት በበለጸገች በዚያች ለም ምድር ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንላችኋል፤ ትበዛላችሁም።

4 “እስራኤል ሆይ! ይህን አስታውስ! እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤

5 እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤

6 ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች አትርሳ፤

7 እነዚህኑ ትእዛዞች ለልጆችህ አስተምራቸው፤ በቤት ስትቀመጥም ሆነ በመንገድ ስትሄድ፥ ዕረፍት በምታደርግበትም ጊዜ ሆነ ሥራ በምትሠራበት ጊዜ ሁሉ፥ እነዚህን ትእዛዞች ዘወትር አሰላስል፤

8 ምልክት ይሆኑህ ዘንድ በእጅህ ላይ እሰራቸው፤ በግንባርህም እንደ መለያ ለጥፋቸው።

9 በቤትህ ደጃፍ መቃኖችና በቅጽር በሮችህ ላይ ጻፋቸው።


ስላለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

10 “እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ በገባላቸው የተሰፋ ቃል መሠረት አንተ ያልገነባሃቸው ታላላቅና የሚያማምሩ ከተሞች ያሉበትን ምድር ይሰጥሃል።

11 የምትወርሳቸው ቤቶች አንተ ባላኖርከው መልካም ነገር የተሞሉ ይሆናሉ፤ ያልቈፈርካቸውም የውሃ ጒድጓዶች በዚያ ይገኛሉ፤ እንዲሁም አንተ ያልተከልካቸው የወይን ተክሎችና የወይራ ዛፎች ይገኛሉ፤ እግዚአብሔር ወደዚህች ምድር አስገብቶህ በልተህ በምትጠግብበት ጊዜ፥

12 ባሪያ ሆነህ ትኖርባት ከነበረችው ከግብጽ ምድር ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ጥንቃቄ አድርግ።

13 አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት አክብረው፤ እርሱን ብቻ አምልክ፤ መሐላህም በእርሱ ስም ብቻ ይሁን።

14 በዙሪያችሁ ያሉ አሕዛብ የሚሰግዱላቸውን ሌሎችን ባዕዳን አማልክት አታምልኩ፤

15 ባዕዳን አማልክትን ብታመልኩ በመካከላችሁ የሚገኘውን የአምላካችሁን ቊጣ ታስነሣላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆነ ከምድር ገጽ ጠራርጎ ያጠፋችኋል፤

16 “ ‘ማሳህ’ ተብሎ በሚጠራው ቦታ እንዳደረጋችሁት ዐይነት እግዚአብሔር አምላካችሁን አትፈታተኑ፤

17 እርሱ ያዘዛችሁንም ትእዛዞች፥ ድንጋጌዎችና ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ጠብቁ።

18 በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክልና መልካም የሆነውን ሁሉ አድርግ፤ ይህን ብታደርግ ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ ይከናወንልሃል፤ እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ በገባውም ተስፋ ቃል መሠረት መልካሚቱን ምድር ትወርሳለህ፤

19 ይህንንም የምታደርገው ጌታ በሰጠህ ተስፋ መሠረት ጠላቶችህን ሁሉ በማባረር ነው።

20 “በሚመጡት ዘመናት ልጅህ የእነዚህ ሕግጋት፥ ደንቦችና ሥርዓቶች ትርጒም ምንድን ነው ብሎ ሲጠይቅህ

21 በዚያን ጊዜ አንተ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘ቀድሞ እኛ ለግብጽ ንጉሥ ባርያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔር ግን በታላቅ ኀይሉ አወጣን፤

22 ግብጻውያንን፥ ንጉሣቸውንና መኰንኖቻቸውን በብርቱ የሚጐዱ ታላላቅ ተአምራትን ማድረጉን በገዛ ዐይኖቻችን ዐይተናል፤

23 ያወርሳቸው ዘንድ ለቀድሞ አባቶቻችን በገባው የተስፋ ቃል መሠረት ወደዚህ አምጥቶ ይህችን ምድር ሊሰጠን ከግብጽ ነጻ አወጣን።

24 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር አምላካችን እነዚህን ደንቦች እንድንፈጽምና እርሱንም እንድንፈራው አዞናል፤ እኛም ይህን ብናደርግ እርሱ ዘወትር ሁሉ ነገር በመልካም ሁኔታ እንዲከናወንልን ያደርጋል፤ ዛሬ እንደሚያደርገውም ሁሉ በሕይወት ያኖረናል፤

25 እግዚአብሔር አምላካችን እንዳዘዘን የእርሱን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብንፈጽም ለእኛ ጽድቅ ይሆንልናል።’

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች