ዘዳግም 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሙሴ ዐሥሩን ትእዛዞች እንደገና መቀበሉ ( ዘፀ. 34፥1-10 ) 1 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ቀድሞ የተሰበሩትን የድንጋይ ጽላቶች አስመስለህ በምትካቸው ሁለት ጽላቶች ቅረጽ፤ ለእነርሱ ማኖሪያ የሚሆን ታቦትም ከእንጨት ሥራ፤ እኔም ወዳለሁበት ተራራ ውጣ፤ 2 ቀድሞ በሰበርካቸው ጽላቶች ላይ የነበሩትን ትእዛዞች እንደገና እጽፍባቸዋለሁ፤ አንተም በታቦቱ ውስጥ ታኖራቸዋለህ።” 3 “ስለዚህም እኔ ከግራር እንጨት ታቦትን ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹ ያሉትንም የድንጋይ ጽላቶች በመቅረጽ አዘጋጀሁ፤ እነርሱንም በእጄ ይዤ ወደ ተራራው ወጣሁ፤ 4 እግዚአብሔርም በተራራው ግርጌ ተሰብስባችሁ በነበረበት ቀን በእሳት ውስጥ ሆኖ የገለጠላችሁን ዐሥሩን ትእዛዞች እንደ ቀድሞው ጽሑፍ አድርጎ በአሁኖቹ ጽላቶች ላይ ጻፈ፤ ጽላቶቹንም ለእኔ ሰጠኝ፤ 5 እኔም ከተራራው ተመልሼ በመውረድ እግዚአብሔር ባዘዘኝ መሠረት ጽላቶቹን በሠራሁት ታቦት ውስጥ አኖርኳቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እነሆ፥ በዚያው ውስጥ ይገኛሉ።” 6 (እስራኤላውያንም ከቤን ያዕቃን የውሃ ጒድጓዶች ተነሥተው ወደ ሞሴራ ተጓዙ፤ አሮንም በዚያው ሞቶ ተቀበረ፤ በእርሱም ምትክ ልጁ አልዓዛር ካህን ሆነ። 7 ከዚያም ተነሥተው ጉድጎዳ ተብሎ ወደሚጠራ ስፍራ ተጓዙ፤ ከዚያም የውሃ ፈሳሾች ወደሚገኙበት ወደ ዮጥባታ አመሩ፤ 8 በዚያን ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት እንዲሸከሙ፥ በፊቱም በመቆም እንዲያገለግሉትና ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም እንዲባርኩ የሌዊን ነገድ በመለየት ሾመ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የሌዊ ነገድ ትውልድ አገልግሎት ይኸው ነው። 9 የሌዊ ነገድ ከሌሎቹ ወንድሞቹ ጋር ርስት እንዲኖረው ያልተደረገበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ አስቀድሞ እንደ ተናገረ ካህናት ሆነው የማገልገልን መብት በማግኘታቸው ራሱ እግዚአብሔር ለሌዋውያን ርስታቸው ነው።) 10 “እኔም ከዚህ በፊት ባደረግሁት ዐይነት እንደገና በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጸለይ ቈየሁ፤ እግዚአብሔርም እንደገና ልመናዬን ሰምቶ አንተን ላለማጥፋት ፈቀደ። 11 ከዚህም በኋላ ‘እንግዲህ ሂድ፤ ለቀድሞ አባቶቻቸው በሰጠሁት የተስፋ ቃል መሠረት ምድሪቱን እንዲወርሱ ሕዝቡን ምራ’ አለኝ። ከእናንተ የሚፈለገው እግዚአብሔርን መፍራት ነው 12-13 “እንግዲህ እስራኤል ሆይ! እግዚአብሔር አምላክህን እንድትፈራው፥ በመንገዱ ሁሉ እንድትሄድ፥ እንድትወደው በሙሉ ልብህና በሙሉ ሐሳብህ እንድታመልከው፥ ለደኅንነትህ ሲባል እኔ ዛሬ የማዝህን የእግዚአብሔር አምላክህን ትእዛዝና ድንጋጌ እንድትጠብቅ ነው እንጂ እርሱ ሌላ ከአንተ ምን ይፈልጋል? 14 ሰማይና ከሰማይ በላይ ያሉ ሰማያት፥ ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ማናቸውም ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። 15 እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶችህ የነበረው ፍቅር እጅግ ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ፥ ዛሬም አንተን ከብዙ አሕዛብ መካከል መርጦአል፤ አንተም እስከ አሁን የእርሱ ምርጥ ሕዝብ ነህ። 16 ስለዚህም ከአሁን በኋላ ልበ ደንዳናነትንና እልኸኛነትን አስወግዳችሁ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሁኑ፤ 17 እግዚአብሔር አምላካችሁ ከባዕዳን አማልክት ሁሉና ከኀይላትም ሁሉ በላይ ታላቅና ብርቱ ስለ ሆነ በፍርሃት መከበር ይገባዋል። እርሱ በፍርድ አያዳላም፤ ጉቦም አይቀበልም። 18 እርሱ እናትና አባት ለሌላቸው ድኻ አደጎችና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች በትክክል ይፈርዳል፤ እርሱ በእኛ ሕዝብ መካከል የሚኖሩትንም መጻተኞች ሁሉ ስለሚወድ ምግብና ልብስ ይሰጣቸዋል። 19 ስለዚህም እናንተም ለእነዚህ ስደተኞች ፍቅራችሁን ልታሳዩአቸው ይገባል፤ እናንተም ራሳችሁ በግብጽ ምድር መጻተኞች የሆናችሁበት ጊዜ ነበር። 20 አምላክህን እግዚአብሔርን በመፍራት ለእርሱ ታዘዝ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ ለእርሱ ታማኝ ሆነህ በእርሱ ስም ብቻ ማል። 21 እርሱ አምላክህ ነው፤ እርሱ ለአንተ ያደረገልህን ታላላቅና አስደናቂ ነገሮችን ሁሉ በገዛ ዐይኖችህ ስላየህ ዘወትር አመስግነው። 22 የቀድሞ አባቶችህ ወደ ግብጽ በወረዱ ጊዜ ብዛታቸው ሰባ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር አምላክህ የአንተን ቊጥር ብዛት እንደ ሰማይ ከዋክብት አድርጎታል። |