2 ሳሙኤል 7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምናታን ለዳዊት የተናገረው ቃል ( 1ዜ.መ. 17፥1-15 ) 1 እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉ ስለ ጠበቀው ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ በሰላም ይኖር ነበር። 2 ከዚህም በኋላ ንጉሡ ነቢዩ ናታንን “እነሆ እኔ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል!” አለው። 3 ናታንም “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ በልብህ ያሰብከውን ሁሉ አድርግ” ሲል መለሰለት። 4 ነገር ግን በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ናታንን እንዲህ አለው፤ 5 “ሂድና ለአገልጋዬ ለዳዊት እኔ ስለ እርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ የምኖርበትን ቤተ መቅደስ የምትሠራልኝ አንተ ነህን? 6 የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ በመታደግ ካዳንኩበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ በድንኳን ውስጥ ሆኜ በየስፍራው ስዘዋወር ኖርኩ እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም፤ 7 ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ ሁሉ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው መሪዎች መካከል በሊባኖስ ዛፍ እንጨት ቤት እንዲሠራልኝ የጠየቅሁት አለን?’ 8 “ስለዚህም ለአገልጋዬ ለዳዊት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እኔ አንተን የበግ መንጋ ከምትጠብቅበት መስክ አንሥቼ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ፤ 9 በሄድክበት ስፍራ ሁሉ እኔ ከአንተ ጋር ነበርኩ፤ ወደፊትም በተራመድህ መጠን ጠላቶችህን ድል አደረግሁልህ፤ ገና ደግሞ በዓለም እንደ ታወቁት ታላላቅ መሪዎች ዝነኛ አደርግሃለሁ። 10-11 ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ አዘጋጅቴ በራሳቸው ቦታ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ለእነርሱ መሳፍንትን ከሾምኩበት ጊዜ ጀምሮ ክፉ አድራጊዎች ቀድሞ ያደርጉት እንደ ነበረው አያስጨንቋቸውም፤ አንተንም ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ከቤትህ አልጋህን የሚወርሱ ልጆች እተካልሃለሁ ብሎ ይገልጥልሃል። 12 ዘመንህ ተፈጽሞ ከቀድሞ አባቶችህ ጋር በምታርፍበት ጊዜ ከአብራክህ የሚወጣውን ልጅህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ የእርሱንም መንግሥት አጸናለሁ። 13 ለስሜ መጠሪያ ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ። 14 እኔ አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጄ ይሆናል፤ ስሕተት በሚፈጽምበትም ጊዜ አባት ልጁን እንደሚቀጣ እቀጣዋለሁ፤ 15 ይሁን እንጂ በእርሱ ቦታ አንተ ትነግሥ ዘንድ ባስወገድኩት በሳኦል ላይ እንዳደረግሁ ዘለዓለማዊ ፍቅሬን ከልጅህ አላርቅም። 16 ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ይጠነክራል፤ ዙፋንህም ለዘለዓለም የጸና ይሆናል።’ ” 17 በዚህም ቃልና ራእይ ሁሉ መሠረት ናታን ለዳዊት ገለጠለት። ዳዊት ለእግዚአብሔር ያቀረበው የምስጋና ጸሎት ( 1ዜ.መ. 17፥16-27 ) 18 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝ፤ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ ምንድን ነው? 19 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህም በዐይንህ ፊት ያነሰ ሆኖ አሁንም የበለጠ ነገር እያደረግህ ነው፤ ስለ ባሪያህ ልጆች ለሚመጡት ዘመናት ብዙ የተስፋ ቃል ተናግረሃል፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ይህ ለሰው ሁሉ የተለመደ ድርጊትህ ነውን? 20 እንግዲህ ምን ልልህ እችላለሁ? እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እኔን ባሪያህን ታውቀኛለህ። 21 ይህን ታላቅ ነገር በቃልህ መሠረትና እንደ ልብህ ፈቃድ ያደረግኸው አገልጋይህ ያውቅ ዘንድ ነው። 22 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፤ እንደ አንተ ማንም የለም፤ በሰማነው መሠረት ከአንተ በቀር አምላክ የለም። 23 ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ያድን ዘንድ፥ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ ተአምራትንና ድንቅ ነገሮችን ያደርግ ዘንድ፥ ሕዝቦችንና አማልክቶቻቸውን በፊታቸው ያስወግድ ዘንድ እግዚአብሔር ከግብጽ ባርነት እንዳዳነው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? 24 እስራኤልንም ለዘለዓለም ሕዝብህ አደረግህ፤ ጌታ ሆይ፥ አንተም አምላካቸው ሆንክ። 25-26 “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ስለ እኔና ስለ ዘሮቼ የተናገርከውን የተስፋ ቃል ሁሉ ለዘለዓለም ፈጽም፤ ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሆን ዘንድ የተናገርከውን ፈጽም፤ ሰዎችም ልዑል እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይላሉ። የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል። 27 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ ለአገልጋይህ ቤት እሠራለሁ ብለህ ስለ ገለጥክለት አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት አግኝቶአል። 28 “አሁንም ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህ ታማኝ ነው፤ እነሆ፥ አሁንም ይህን መልካም የተስፋ ቃል ለአገልጋይህ ሰጥተሃል። 29 በፊትህ ለዘለዓለም ይኖር ዘንድ የአገልጋይህን ቤት ለመባረክ ፈቃድህ ይሁን፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! አንተ በበረከትህ እንደ ተናገርክ የአገልጋይህ ቤት ለዘለዓለም የተባረከ ይሁን።” |