2 ሳሙኤል 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱ ( 1ዜ.መ. 13፥1-14 ፤ 15፥25—16፥6፤43 ) 1 ዳዊት እንደገና ከመላው እስራኤል የተመረጡ በድምሩ ሠላሳ ሺህ የሚሆኑ ምርጥ ወታደሮች በአንድነት አሰባሰበ፤ 2 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በኪሩቤል ላይ ዙፋኑን የዘረጋውን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የቃል ኪዳኑን ታቦት ለማምጣት ወደ በዓለ ይሁዳ ሄዱ። 3 እነርሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት በኮረብታ ላይ ከሚገኘው ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው በአዲስ ሠረገላ ላይ አኖሩት፤ ዑዛና አሕዮ ተብለው የሚጠሩት የአቢናዳብ ልጆች ሠረገላውን እየመሩ በሚጓዙበት ጊዜ፥ 4 አሕዮ ከታቦቱ ፊት ቀድሞ ይሄድ ነበር። 5 ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ የበገና፥ የመሰንቆ፥ የከበሮ፥ የጸናጽልና የቃጭል ድምፅ እያሰሙ ለእግዚአብሔር ክብር በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ያሸበሽቡ ነበር። 6 ናኮን ተብሎ ወደሚጠራውም አውድማ በደረሱ ጊዜ ሠረገላውን የሚስቡት በሬዎች ስለ ነቀነቁት ዑዛ እጁን ዘርግቶ የቃል ኪዳኑ ታቦት እንዳይወድቅ ደገፈ፤ 7 እግዚአብሔር አምላክም ወዲያውኑ ተቈጥቶ ስለ ድፍረቱ ዑዛን ገደለው፤ ስለዚህም ዑዛ በዚያው በቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ ሞተ፤ 8 ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የዚያ ስፍራ ስም “ፌሬጽዑዛ” እየተባለ ሲጠራ ይኖራል፤ እግዚአብሔር በቊጣ ተነሣሥቶ ዑዛን በመግደሉ ዳዊት እጅግ ተበሳጨ። 9 ከዚያም በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “እንዲህ ከሆነማ የቃል ኪዳኑን ታቦት እንዴት ልወስደው እችላለሁ?” አለ። 10 ስለዚህም ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ላለመውሰድ ወሰነ፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ ከመንገድ መልሶ የጋት ከተማ ነዋሪ ወደ ሆነው ዖቤድኤዶም ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ቤት አስገባው፤ 11 እዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ዖቤድኤዶምንና ቤተሰቡን ባረከ። 12 በቃል ኪዳኑ ታቦት ምክንያት እግዚአብሔር የዖቤድኤዶምን ቤተሰብና ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የባረከለት መሆኑን ንጉሥ ዳዊት ሰማ፤ ስለዚህም የቃል ኪዳኑን ታቦት በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወስደው በማሰብ ወደ ዖቤድኤዶም ቤት ሄዶ አወጣው። 13 የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሰዎች ስድስት እርምጃ በተራመዱ ቊጥር ዳዊት እንደገና እያስቆመ አንድ ወይፈንና አንድ የሰባ ፍሪዳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። 14 ዳዊት ከበፍታ የተሠራ ሽርጥ በወገቡ ዙሪያ ታጥቆ እግዚአብሔርን በማክበር በሙሉ ኀይሉ ያሸበሽብ ነበር፤ 15 በዚህም ዐይነት ዳዊትና መላው እስራኤል በደስታ እልል እያሉና የእምቢልታ ድምፅ እያሰሙ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ሄዱ። 16 ታቦቱን ይዘው ወደ ከተማ በሚገቡበት ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ተመለከተች፤ ንጉሡ ዳዊት እየዘለለ ሲያሸበሽብ አይታም በልብዋ ናቀችው፤ 17 ታቦቱንም አምጥተው ዳዊት ባዘጋጀለት ድንኳን ውስጥ በተመደበለት ስፍራ አኖሩት፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ። 18 መሥዋዕት ማቅረቡንም በፈጸመ ጊዜ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን መረቀ፤ 19 ለሁሉም ምግብ አደላቸው፤ በእስራኤል ለሚገኘው ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት አንዳንድ ኅብስት፥ አንዳንድ ቊራጭ የተጠበሰ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚያም በኋላ ሁሉም ወደየቤታቸው ሄዱ። 20 ከዚያም በኋላ ዳዊት ቤተሰቡን ሰላም ለማለት ወደ ቤት ገባ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ልትቀበለው ወጣችና “የእስራኤል ንጉሥ ዛሬ ትልቅ ስም አግኝቶአል! በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ ቅሌታም ሽማግሌ እርቃኑን ገልጦአል!” አለችው። 21 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “እኔ ያሸበሸብኩት የሕዝቡ የእስራኤል መሪ ያደርገኝ ዘንድ በአባትሽና በቤተሰቡ ፈንታ ለመረጠኝ እግዚአብሔር ክብር ነው፤ አሁንም ቢሆን እርሱን ለማክበር ከመጨፈር አልገታም፤ 22 ከዚህም የባሰ ራሴን አዋርዳለሁ፤ ለአንቺ እንደሚመስልሽ በዐይንሽ ፊት የተናቅሁ ብሆንም በእነርሱ ፊት ራስህን አዋረድክ ብለሽ በተናገርሽባቸው ልጃገረዶች ዘንድ እጅግ የተከበርኩ እሆናለሁ!” 23 ከዚህም የተነሣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም። |