2 ሳሙኤል 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምአምኖንና ትዕማር 1 የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ውብ የሆነች ትዕማር ተብላ የምትጠራ፥ ገና ባል ያላገባች እኅት ነበረችው፤ አምኖን ተብሎ የሚጠራው ከዳዊት ልጆች አንዱ ትዕማርን ወደዳት፤ 2 እርስዋንም እጅግ ከማፍቀሩ የተነሣ ታመመ፤ ድንግል ስለ ነበረች እርስዋን መገናኘት ከቶ አልተቻለውም። 3 ነገር ግን በጣም ዘዴኛ የሆነ፥ ዮናዳብ ተብሎ የሚጠራ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ነበር፤ 4 ዮናዳብ አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ ሆነህ ሳለ በየቀኑ ሰውነትህ ጠውልጎ የማይህ ስለምንድን ነው? እስቲ ንገረኝ” ሲል ጠየቀው። አምኖንም “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን ስለ ወደድኩ ነው” ሲል መለሰለት። 5 ዮናዳብም እንዲህ አለው፤ “ይህ ከሆነ እንግዲህ የታመምህ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣ፥ ‘እኅቴ ትዕማርን መጥታ እንድታስታምመኝ እባክህ ንገራት፤ እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ምግብ አዘጋጅታ እርስዋ ራስዋ እንድታጐርሰኝ እፈልጋለሁ’ በለው።” 6 ስለዚህም አምኖን የታመመ በመምሰል በአልጋው ላይ ተኛ። ንጉሥ ዳዊትም ሊጠይቀው ወደ እርሱ በሄደ ጊዜ አምኖን “እኅቴ ትዕማር እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ሁለት እንጀራ ጋግራ እርስዋ ራስዋ እንድታቀርብልኝ ፍቀድላት” አለው። 7 ስለዚህም ዳዊት በቤተ መንግሥት ለምትገኘው ለትዕማር “ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ አዘጋጂለት” የሚል ትእዛዝ ላከ። 8 እርስዋም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት በሄደች ጊዜ አልጋ ላይ ተኝቶ አገኘችው፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ በማቅጠንም አምኖን እያያት እንጀራ ጋገረች፤ 9 የጋገረችውንም እንጀራ ከምጣዱ አውጥታ እንዲበላ አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መመገቡን እምቢ ብሎ “ሰዎቹን ሁሉ አስወጡልኝ” አለ፤ ሁሉም ወጡ፤ 10 ከዚያም በኋላ አምኖን ትዕማርን “ታጐርሺኝ ዘንድ ምግቡን ይዘሽ ወደ አልጋዬ አምጪው” አላት፤ ስለዚህም ትዕማር ምግቡን ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን አመጣችው። 11 በምታቀርብለትም ጊዜ አፈፍ በማድረግ ይዞ “እኅቴ ሆይ! አብረን እንተኛ!” አላት። 12 እርስዋም “አይሆንም ወንድሜ ሆይ! እባክህ አታዋርደኝ! የዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ተግባር በእስራኤል ተፈጽሞ አያውቅም! ስለዚህ ይህን ትልቅ ብልግና አትፈጽም፤ 13 እንደዚህ ካዋረድከኝ በኋላ በሕዝብ ፊት ራሴን ቀና አድርጌ ለመሄድ እንዴት እችላለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል እጅግ የተዋረድክ ትሆናለህ፤ ይልቅስ ለንጉሡ ብትነግረው እኔን ለአንተ በሚስትነት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ነኝ” አለችው። 14 እርሱ ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ እርሱም ከእርስዋ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበረ በኀይል አስገድዶ ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ። 15 ከዚያም በኋላ አምኖን እጅግ አድርጎ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት ይበልጥ አሁን በእርስዋ ላይ ያለው ጥላቻ ስለ ባሰ “ከዚህ ውጪልኝ!” አላት። 16 እርስዋም “አይሆንም! እኔን እንደዚህ አድርገህ ብታባርረኝ አሁን ከፈጸምከው በደል ይልቅ የከፋ ኃጢአት ትፈጽማለህ!” አለችው። አምኖን ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ 17 የግል አገልጋዩንም ጠርቶ “ይህችን ሴት ከፊቴ ወዲያ አስወግድልኝ! እርስዋንም ወደ ውጪ አስወጥተህ በሩን ዝጋ!” አለው። 18-19 ትዕማርም የአምኖን አሽከር ከቤት አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ በዚያን ዘመን ያላገቡ የነገሥታት ልጆች ይለብሱት የነበረውን እጅጌ ረዥም የነበረ መጐናጸፊያ ለብሳ ነበር፤ እርስዋም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ ለብሳው የነበረውን መጐናጸፊያ ቀዳ እጅዋን በራስዋ ላይ በመጫን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች። 20 ወንድምዋ አቤሴሎም ባያት ጊዜ “እኅቴ ሆይ! ወንድምሽ አምኖን አስነወረሽን? እባክሽ እንደዚህ አትበሳጪ፤ እርሱ ወንድምሽ ስለ ሆነ ለማንም አትናገሪ” አላት። ስለዚህ ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ከሰው የተለየች ብቸኛ ሆና ተቀመጠች። 21 ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ በብርቱ ተቈጣ፤ [ነገር ግን ይወደው ስለ ነበርና የበኲር ልጁም ስለ ነበረ ልጁን አምኖንን ሊያሳዝነው አልፈለገም።] 22 የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና በመድፈሩም ምክንያት አቤሴሎም አምኖንን እጅግ ጠላው፤ ዳግመኛም ክፉም ሆነ ደግ ሊያነጋግረው አልፈለገም። አቤሴሎም የወሰደው የበቀል እርምጃ 23 ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ከተማ አጠገብ በዓለ ሐጾር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ስለዚህም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ ለግብዣ ወደዚያ ጠራ። 24 ወደ ንጉሥ ዳዊትም ሄዶ “ንጉሥ ሆይ! በጎቼን እየሸለትሁ ነው፤ ስለዚህ አንተና መኳንንትህ መጥታችሁ የግብዣው ተካፋዮች እንድትሆኑልኝ ትፈቅዳለህን?” አለው። 25 ንጉሡም “ልጄ ሆይ! መምጣት አያስፈልገንም፤ እኛ ሁላችን ከመጣን መስተንግዶው ይከብድብሃል” ሲል መለሰለት፤ አቤሴሎምም አጥብቆ ጠየቀ፤ ንጉሡ ግን አሳቡን መለወጥ ስላልፈቀደ አቤሴሎምን መርቆ አሰናበተው። 26 አቤሴሎም ግን “መልካም ነው! አንተ መምጣት ካልፈቀድህ ወንድሜ አምኖን እንዲመጣ አትፈቅድለትምን?” ሲል ጠየቀ። ንጉሡም “እርሱስ ቢሆን ለምን ይመጣል?” ሲል ጠየቀው። 27 አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ጠየቀ ዳዊት፥ አምኖንና የቀሩትም ወንዶች ልጆቹ ሁሉ እንዲሄዱ ፈቀደ። አቤሴሎም ለንጉሥ የሚገባ ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር፤ 28 አገልጋዮቹንም “አምኖን ብዙ ጠጥቶ መስከሩን ተመልከቱ፤ እኔም ትእዛዝ በምሰጣችሁ ጊዜ ግደሉት፤ ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ እኔ ስለ ሆንኩ ከቶ አትፍሩ! ደፋሮች ሁኑ፤ ምንም አታመንቱ!” አላቸው። 29 ስለዚህ አገልጋዮቹ አቤሴሎም በነገራቸው መመሪያ መሠረት አምኖንን ገደሉ፤ የቀሩትም የዳዊት ወንዶች ልጆች በበቅሎዎቻቸው ተቀምጠው እየጋለቡ ሸሹ። 30 ወደ ቤታቸው ለመድረስ ገና በመንገድ ላይ ሳሉ “አቤሴሎም ልጆችህን ሁሉ ገደላቸው! አንድ እንኳ የቀረ የለም!” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። 31 ንጉሡ ከተቀመጠበት በመነሣት በሐዘን ልብሱን ቀዶ በመሬት ላይ ተዘረረ፤ በዚያ ከእርሱ ጋር የነበሩ አገልጋዮቹም በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው በአጠገቡ በአክብሮት ቆሙ። 32 የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ! የተገደሉት ልዑላኑ በሙሉ አይደሉም፤ የተገደለው አምኖን ብቻ ነው፤ አቤሴሎም ይህን ለማድረግ ያቀደው አምኖን የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና ከደፈረበት ጊዜ አንሥቶ እንደ ነበር ፊቱን አይተህ መረዳት ትችላለህ። 33 አሁንም ልዑላን በሙሉ እንደ ተገደሉ ሆኖ የተነገረህን ወሬ አትመን። የተገደለው አምኖን ብቻ ነው።” 34 በዚህም ጊዜ አቤሴሎም ሸሽቶ አምልጦ ነበር፤ ለዘብ ጥበቃ ተረኛ የነበረውም ወታደር ልክ በዚያን ሰዓት ከሖርናይም ወደዚህ በሚመጣው መንገድ ላይ ካለው ኮረብታ ብዙ ሕዝብ ወደ ታች ሲወርድ አየ፤ ወደ ንጉሡም ቀርቦ ያየውን ሁሉ ተናገረ፤ 35 ዮናዳብም ዳዊትን “ልክ እኔ አገልጋይህ እንዳልኩት እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤” አለው። 36 እርሱ ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የዳዊት ልጆች ገብተው መላቀስ ጀመሩ፤ ዳዊትና መኳንንቱም በመረረ ሁኔታ አለቀሱ። 37-38 አቤሴሎምም ሸሽቶ የገሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ፤ በዚያም ሦስት ዓመት ቈየ፤ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አምኖን ሞት ለረዥም ጊዜ በማዘን አለቀሰ፤ 39 ነገር ግን ስለ አምኖን ሞት የነበረበት ሐዘን እየተረሳ በሄደ ቊጥር ልጁን አቤሴሎምን መናፈቅ ጀመረ። |