Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ጴጥሮስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የጌታ ኢየሱስ የመምጣት ተስፋ

1 ወዳጆች ሆይ! ይህ የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፤ ሁለቱንም መልእክቶች የጻፍኩላችሁ እነዚህን ነገሮች በማስታወስ ቅን አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ላነቃቃችሁ ብዬ ነው።

2 ከዚህ በፊት ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና በእናንተ ሐዋርያት አማካይነት ያገኛችሁትን የጌታችንንና የአዳኛችንን ትእዛዝ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ።

3 ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያፌዙና ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ፤

4 እነርሱ “ጌታ ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተሰጥቶ አልነበረምን? ታዲያ፥ የት አለ? የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ ሁሉ ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እንደ ነበረው ነው” ይላሉ።

5 እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማይ በእግዚአብሔር ቃል መፈጠሩን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው ይክዳሉ።

6 በዚያን ጊዜ የነበረውም ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ።

7 እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች አሁን ያሉት ሰማይና ምድር እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቈያሉ።

8 ወዳጆቼ ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ።

9 አንዳንድ ሰዎች እንደሚመስላቸው ጌታ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም ሰው እንዳይጠፋ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሣል።

10 የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል፤

11 እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ ታዲያ፥ እናንተ በቅድስናና እግዚአብሔርን በማምለክ መኖር እንዴት አይገባችሁም?

12 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና በቶሎም እንዲመጣ የምትሠሩ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማይ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል፤ ፍጥረቶችም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤

13 ነገር ግን እኛ በሰጠን ተስፋ መሠረት የጽድቅ ሥራ የሚመሠረትበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን።

14 ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህ ሁሉ የሚሆንበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ካላችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤

15 የጌታችንም መታገሥ ለእናንተ መዳን መሆኑን ዕወቁ፤ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስም በተሰጠው ጥበብ መጠን የጻፈላችሁ ይህንኑ ነው።

16 እርሱ ስለዚህ ጉዳይ በመልእክቶቹ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ጽፎአል፤ በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ወላዋዮች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህንም ነገሮች ያጣምማሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ለጥፋታቸው ነው።

17 እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! ይህን አስቀድማችሁ ስላወቃችሁ በዐመፀኞች ስሕተት ተስባችሁ ከጽኑ አቋማችሁ እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤

18 ይልቅስ በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እርሱንም በማወቅ ከፍ ከፍ በሉ፤ ለእርሱ አሁንም ለዘለዓለምም ክብር ይሁን! አሜን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች