2 ነገሥት 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ መዳን ( ኢሳ. 38፥1-8 ፤ 21-22 ፤ 2ዜ.መ. 32፥24-26 ) 1 በዚያን ዘመን ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና ታሞ ለመሞት ተቃርቦ ነበር፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ሊጐበኘው ሄዶ “እግዚአብሔር ‘ከሕመምህ አትድንም፤ መሞትህም ስለማይቀር ሁሉን ነገር አስተካክል’ ብሎሃል” ሲል ነገረው። 2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ፥ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፦ 3 “እግዚአብሔር ሆይ! በታማኝነትና በቅንነት እንዳገለገልኩህ፥ አንተ የምትደሰትበትንም ነገር ለማድረግ ዘወትር እጥር እንደ ነበር ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ!” እያለ በመጸለይ ምርር ብሎ አለቀሰ። 4 ኢሳይያስ ከንጉሡ ፊት ወጥቶ የቤተ መንግሥቱን መካከለኛ አደባባይ አልፎ ከመሄዱ በፊት፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፦ 5 “ሕዝቤን ወደሚመራው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ተመልሰህ በመግባት እንዲህ በለው፦ ‘እኔ የቀድሞ አባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም ተመልክቻለሁ፤ እኔ እፈውስሃለሁ፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ትወጣለህ፤ 6 በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ፤ አንተንና ይህችን የኢየሩሳሌምን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ በመታደግ አድናለሁ፤ ስለ ክብሬና ለአገልጋዬ ለዳዊት ስለ ሰጠሁት የተስፋ ቃል ከተማይቱን በመከላከል እጠብቃታለሁ።’ ” 7 ከዚህም በኋላ ኢሳይያስ የንጉሡን አገልጋዮች፥ “የበለስ ፍሬ ጥፍጥፍ አምጡልኝ” ብሎ አመጡለት፤ በቊስሉ ላይ ባደረጉለት ጊዜ የሕዝቅያስ ቊስል ተፈወሰ። 8 ንጉሥ ሕዝቅያስም ኢሳይያስን “እግዚአብሔር እንደሚፈውሰኝና ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ እንደምችል በምን ምልክት ዐውቃለሁ?” ሲል ጠየቀው። 9 ኢሳይያስም “እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም ስለ መሆኑ ራሱ ምልክት ይሰጥሃል፤ እንግዲህ አሁን የምትመርጠው ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ነው? ወይስ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ?” ሲል ጠየቀው። 10 ሕዝቅያስም “ጥላው ዐሥር ደረጃ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ ይቀላል፤ ስለዚህ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርግልኝ” አለው። 11 ኢሳይያስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ንጉሥ አካዝ ባሠራው ደረጃ ላይ ያረፈው ጥላ ዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ። ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች ( ኢሳ. 39፥1-8 ) 12 በዚያኑ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የባላዳን ልጅ መሮዳክ ባላዳን፥ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታሞ የነበረ መሆኑን ሰማ፤ ስለዚህም ከገጸ በረከት ጋር ደብዳቤ ላከለት፤ 13 ሕዝቅያስም መልእክተኞቹን በደስታ ተቀበላቸው፤ በቤተ መንግሥቱም የዕቃ ግምጃ ቤት ያለውን ሀብት በሙሉ፥ ብሩንና ወርቁን፥ ቅመማ ቅመሙንና ሽቶውን፥ የጦር መሣሪያውንም ሁሉ አሳያቸው፤ በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤትም ሆነ በመንግሥቱ በማንኛውም ስፍራ ካለው ሀብት ሁሉ ሕዝቅያስ ያላሳያቸው አንድም አልነበረም። 14 በዚያን ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ሄዶ፥ “እነዚህ ሰዎች ከወዴት መጡ? ምንስ ነገሩህ?” ብሎ ጠየቀው። ሕዝቅያስም “እነርሱ የመጡት ባቢሎን ከሚባል ከሩቅ አገር ነው” ሲል መለሰለት። 15 ኢሳይያስም “በቤተ መንግሥቱ ምን አዩ” ሲል ጠየቀው። ሕዝቅያስም “ሁሉን ነገር አይተዋል፤ በግምጃ ቤቱ ካለው ሀብት ሁሉ ለእነርሱ ያላሳየኋቸው አንድም ነገር የለም” አለ። 16 ኢሳይያስም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 17 ‘የቀድሞ አባቶችህ እስከዚህች ቀን ያከማቹት በቤተ መንግሥትህ ያለው ሀብት ሁሉ ተጠራርጎ ወደ ባቢሎን የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል፤ ምንም ነገር አይቀርም፤ 18 ከዘሮችህም አንዳንዶቹ ወደ ባቢሎን ተማርከው በመሄድ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ጃንደረቦች ሆነው እንዲያገለግሉ ይደረጋል።’ ” 19 ንጉሥ ሕዝቅያስም በተለይ በእርሱ ዘመን በሰላም የመኖር ዋስትና እንዳለ ስለ ተረዳ “ከእግዚአብሔር ተልከህ የተናገርከኝ ቃል መልካም ነው” ሲል መለሰ። የንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ( 2ዜ.መ. 32፥32-33 ) 20 ንጉሥ ሕዝቅያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ የጀግንነት ሥራው ጭምር፥ እንዲሁም የውሃ ማጠራቀሚያ ግድብ እንዴት እንደ ሠራና ወደ ከተማይቱ ውሃ ለማምጣት ያስቈፈረው የመሬት ውስጥ ቦይ አሠራር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 21 ሕዝቅያስም ሞተ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ምናሴ ነገሠ። |