2 ቆሮንቶስ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለክርስቲያኖች የተደረገ መዋጮ 1 በይሁዳ ላሉት ክርስቲያኖች ስለሚደረገው መዋጮ ልጽፍላችሁ አያስፈልግም፤ 2 “የዐካይያ ሰዎች ከዐለፈው ዓመት ጀምረው ለመርዳት ዝግጁዎች ናቸው” ብዬ በመቄዶንያ ሰዎች ዘንድ ስለ እናንተ የምመካው ትጋታችሁን ስለማውቅ ነው፤ የእናንተም ትጋት ሌሎችን አነሣሥቶአል። 3 በዚህ ነገር በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር እነዚህን ወንድሞች እልካለሁ፤ እናንተም ልክ እኔ ከዚህ በፊት እንዳልኩት ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። 4 የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ወደ እናንተ መጥተው ያልተዘጋጃችሁ ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ በእናንተ በመመካታችን እናፍራለን፤ እናንተማ በጣም ታፍራላችሁ። 5 ስለዚህ ልትሰጡ ቃል የገባችሁበትን የልግሥና ስጦታችሁ በቅድሚያ እንድታዘጋጁ እንዲያስታውሱአችሁ በማለት እነዚህ ወንድሞች ከእኔ ቀድመው ወደ እናንተ እንዲመጡ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ በዚህ ዐይነት እኔ በምመጣበት ጊዜ የልግሥና ስጦታችሁ ዝግጁ ይሆናል፤ እናንተም የምትሰጡት በግድ ሳይሆን በፈቃደኛነት መሆኑን ያሳያል። 6 “ጥቂት የዘራ ጥቂት መከር ይሰበስባል፤ ብዙ የዘራ ብዙ መከር ይሰበስባል” የሚለውን አባባል አስታውሱ። 7 ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወደው በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለ ሆነ እያንዳንዱ ለመስጠት የፈለገውን በልቡ ፈቅዶ በደስታ ይስጥ እንጂ እያመነታ ወይም በግዴታ አይስጥ። 8 ሁልጊዜ በሁሉ ነገር ራሳችሁን ችላችሁ ለመልካም ሥራ ሁሉ ለማዋል እንዲበቃችሁ እግዚአብሔር በብዛት በረከቱን ሊሰጣችሁ ይችላል። 9 ይህም፦ “ለድኾች በልግሥና ሰጠ፤ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። 10 ለዘሪ ዘርን፥ ለምግብ እንጀራን የሚሰጥ አምላክ የምትዘሩትን ዘር አበርክቶ ይሰጣችኋል፤ የልግሥናችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። 11 ልግሥናችሁ በእኛ አማካይነት የሚደርሳቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሁልጊዜ እንድትለግሡ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል። 12 ይህ የምትፈጽሙት የልግሥና አገልግሎት የክርስቲያኖችን ችግር ከማስወገዱም በላይ ሰዎች ለእግዚአብሔር ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል። 13 ይህ የእናንተ የልግሥና አገልግሎት እናንተ የክርስቶስን ወንጌል ተቀብላችሁ ታማኞች መሆናችሁንና ለእነርሱና ለሌሎችም መለገሣችሁን የሚያረጋግጥ ስለ ሆነ ሁሉም እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። 14 እነርሱም እግዚአብሔር ለእናንተ በሰጣችሁ በበለጠ ምክንያት ስለሚያፈቅሩአችሁ ይጸልዩላችኋል። 15 በሰው ቃል ሊነገር ስለማይቻለው ስጦታው እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። |