Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ቆሮንቶስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፥ በቆሮንቶስ ለምትገኘው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንና እንዲሁም በመላው አካይያ ለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ፥

2 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።


ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ያቀረበው ምስጋና

3 ለምሕረት አባትና መጽናናትን ሁሉ ለሚሰጥ እንዲሁም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አባት ለእግዚአብሔር፥ ምስጋና ይሁን።

4 እኛ ከእግዚአብሔር በምናገኘው መጽናናት በመከራ ላይ ያሉትን ሁሉ ማጽናናት እንድንችል እግዚአብሔር እኛን በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።

5 የክርስቶስን መከራ በብዛት እንደ መካፈላችን መጠን እንዲሁም በክርስቶስ መጽናናትን በብዛት እናገኛለን።

6 እኛ መከራ ስንቀበል እናንተ መጽናናትንና መዳንን ታገኛላችሁ፤ እኛ ስንጽናና ደግሞ እናንተም እኛ የምንቀበለውን ዐይነት መከራ በትዕግሥት ተቀብላችሁ ትጽናናላችሁ፤

7 መከራችንን በምትካፈሉበት መጠን መጽናናታችንንም እንደምትካፈሉ ስለምናውቅ በእናንተ ላይ ያለን ተስፋ ጽኑ ነው።

8 ወንድሞች ሆይ! በእስያ ክፍለ ሀገር በነበርንበት ጊዜ የደረሰብንን መከራ እንድታውቁ እንወዳለን፤ ይህም የደረሰብን መከራ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ወድቆብን ስለ ነበር በሕይወት ለመኖር የነበረን ተስፋ እንኳ ተቋርጦ ነበር።

9 እንዲያውም ሞት እንደ ተፈረደብን ያኽል ተሰምቶን ነበር፤ ይህም ሁሉ የደረሰብን፥ የምንተማመነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኀይል አለመሆኑን እንድንገነዘብ ነው።

10 ስለዚህ እርሱ ለሞት ከሚያደርስ አደጋ አድኖናል፤ ያድነናልም፤ ደግሞም እንደሚያድነን ተስፋችን በእርሱ ነው።

11 እናንተም እኛን በጸሎት ልትረዱን ይገባል፤ በብዙ ጸሎት እኛ የእግዚአብሔርን ርዳታ ስናገኝ ብዙ ሰዎች ደግሞ በእኛ ምክንያት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ።


የጳውሎስ ጒብኝት ዕቅድ መለወጥ

12 የምንመካበት ነገር ይህ ነው፤ ይህም እውነት መሆኑን ኅሊናችን ይመሰክርልናል፤ ከሌሎች ሰዎችና በተለይም ከእናንተ ጋር የነበረን ግንኙነት ከእግዚአብሔር ባገኘነው ቅድስናና ቅንነት የተመሠረተ ነው፤ ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነበር እንጂ በሰው ጥበብ አልነበረም።

13 አንብባችሁ ማስተዋል የምትችሉትን ነገር ካልሆነ ሌላ ምንም አንጽፍላችሁም፤ በሙሉ ማስተዋል እንደምትችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፤

14 አሁን ስለ እኛ የምታውቁት በከፊል ነው፤ በኋላ ግን በሙላት እንደምታስተውሉት ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚህም ምክንያት ጌታ ኢየሱስ በሚመጣበት ቀን እኛ በእናንተ እንደምንመካ እናንተም በእኛ ትመካላችሁ።

15 በዚህ ነገር እርግጠኛ ስለ ነበርኩ ሁለት ጊዜ እንድትጠቀሙ ብዬ እናንተን በመጀመሪያ ለመጐብኘት ዐቅጄ ነበር፤

16 ልጐበኛችሁ ያቀድኩትም ወደ መቄዶንያ ሳልፍና ከዚያም በምመለስበት ጊዜ ነበር፤ በዚህም ሁኔታ ወደ ይሁዳ ምድር በማደርገው ጒዞዬ ትረዱኛላችሁ ብዬ አስቤ ነበር።

17 ይህን ባቀድኩ ጊዜ የማደርገውን የማላውቅ ወላዋይ የሆንኩ ይመስላችኋል? ወይስ ይህን በማቀዴ በአንድ ጊዜ “አዎንና አይደለም” እያልኩ በማወላወል በሰው አስተሳሰብ ያደረግኹት ይመስላችኋልን?

18 እግዚአብሔር ታማኝ ስለ ሆነ እኛም የምንነግራችሁ “አዎን ወይም አይደለም” የሚል የማወላወል ቃል አይደለም።

19 እኔና ሲላስ፥ ጢሞቴዎስም የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰበክንላችሁ ሁልጊዜ “አዎን” በሚል ቃል ብቻ እንጂ፥ “አዎን ወይም አይደለም” በሚል አወላዋይ ቃል አልነበረም።

20 እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ሁሉ “አዎን” የሚሆነው በክርስቶስ ነው፤ ስለዚህ ነው ለእግዚአብሔር ክብር በክርስቶስ “አሜን” የምንለው።

21 እኛን ከእናንተ ጋር በክርስቶስ እንድንጸና ያደረገን እግዚአብሔር ነው፤ ለሥራ የለየንም እርሱ ነው፤

22 የእርሱ ለመሆናችን ማስረጃ የሚሆን ማኅተሙን በእኛ ላይ ያደረገና ወደ ፊት ለእኛ ስለሚሰጠን ሀብት በልባችን መንፈስ ቅዱስን እንደ ዋስትና አድርጎ የሰጠን እርሱ ነው።

23 እኔ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሼ ያልመጣሁበት ምክንያት እናንተን እንዳላሳዝናችሁ ለእናንተ በመራራት ነው፤ ለዚሁም እግዚአብሔር ምስክሬ ነው፤

24 እናንተ በእምነታችሁ የጸናችሁ ስለ ሆናችሁ እናንተን ደስ እንዲላችሁ አብረናችሁ እንሠራለን እንጂ በእምነታችሁስ አናዛችሁም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች