1 ጢሞቴዎስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 በአዳኛችን በእግዚአብሔር፥ በተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ፦ 2 በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁንልህ። ከሐሰት ትምህርት ማስጠንቀቁ 3 ወደ መቄዶንያ ስሄድ ሳለሁ ዐደራ እንዳልኩህ እዚያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታደርጋቸው ዘንድ በኤፌሶን ተቀመጥ። 4 ወደ ተረትና መጨረሻ ወደሌለው ወደ ትውልዶች ቈጠራ እንዳይመለሱ እዘዛቸው፤ እነዚህ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉ እንጂ በእምነት ለሚደረገው ለእግዚአብሔር ሥራ አይጠቅሙም። 5 የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፥ ከመልካም ኅሊና፥ ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። 6 አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ተለይተው ወደ ከንቱ ክርክር ተመልሰዋል። 7 ይህንንም የሚያደርጉት የሕግ መምህራን ለመሆን ፈልገው ነው፤ ይሁን እንጂ የሚናገሩትን አያውቁም ወይም እርግጠኞች ነን የሚሉበትንም ነገር አያስተውሉም። 8 ሰው በሚገባ ከሠራበት ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን፤ 9 እንዲሁም ሕግ የተሠራው ለደጋግ ሰዎች እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ሕግ የተሠራው ለዐመፀኞችና ለወንጀለኞች፥ እግዚአብሔርን ለማያመልኩና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና መንፈሳዊ ነገርን ለሚንቁ፥ አባትንና እናትን ለሚገድሉና ለነፍሰ ገዳዮች፥ 10 ለአመንዝሮችና ግብረ ሰዶምን ለሚያደርጉ፥ ሰውን አፍነው በመውሰድ ለሚሸጡ ነጋዴዎችና ለውሸታሞች፥ በሐሰት ለሚምሉና የእውነተኛ ትምህርት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ሁሉ ለሚያደርጉ ነው፤ 11 እውነተኛው ትምህርት ግን የሚገኘው ስለተመሰገነው እግዚአብሔር ከሚያበሥረው ክቡር ወንጌል ነው፤ ይህም ወንጌል ለእኔ በዐደራ የተሰጠኝ ነው። ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት ያቀረበው ምስጋና 12 እኔን ለአገልግሎት በመሾም ታማኝ አድርጎ የቈጠረኝንና የሰጠኝን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አመሰግናለሁ። 13 ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን የሰደብኩና ያሳደድኩ፥ ያዋረድኩም ብሆን፤ እርሱ ምሕረት አደረገልኝ፤ እርሱም ይህን ምሕረት ያደረገልኝ እኔ ይህን ሁሉ ያደረግኹት ባለማወቅና ባለማመን ስለ ነበረ ነው። 14 የአምላካችን ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ ከሆነው እምነትና ፍቅር ጋር ተትረፍርፎ ተሰጠኝ። 15 “ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል እውነተኛና ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ሁሉ የባስሁ ኃጢአተኛ እኔ ነኝ። 16 ነገር ግን ምሕረት ተደረገልኝ፤ ምሕረት የተደረገልኝም ኢየሱስ ክርስቶስ ወሰን የሌለውን ትዕግሥቱን ከሁሉ የባስሁ ኀጢአተኛ በሆንኩት በእኔ ላይ በማሳየቱ በእርሱ ለሚያምኑና የዘለዓለም ሕይወት ለሚያገኙ ምሳሌ እንድሆን ነው። 17 ስለዚህ ለዘለዓለማዊው ንጉሥ፥ ለማይሞተው፥ ለማይታየው፥ ለአንዱ አምላክ ክብርና ምስጋና ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። 18 ልጄ ጢሞቴዎስ ሆይ! ከዚህ ቀደም ስለ አንተ በትንቢት በተነገረው መሠረት የሚከተለውን ትእዛዝ በዐደራ እሰጥሃለሁ፤ ትንቢቱን በመከተል መልካም ጦርነትን ተዋጋ፤ 19 እምነትና መልካም ኅሊና ይኑርህ። አንዳንድ ሰዎች ኅሊናቸውን በመጣላቸው መርከብ በማዕበል እንደሚጠፋ እምነታቸውን አጥፍተዋል። 20 ከእነርሱ መካከል ሄሜኔዎስና እስክንድር ይገኛሉ፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ከመናገር መቈጠብን እንዲማሩ ለሰይጣን አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁ። |