1 ሳሙኤል 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ሳኦልና ዳዊት ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ የሳኦል ልጅ ዮናታን ከዳዊት ጋር እጅግ የተቀራረበ አንድነት መሠረተ፤ እንደ ራሱም አድርጎ ወደደው፤ 2 ከዚያን ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ከእርሱ ጋር እንዲኖር አደረገ፤ ወደ ቤቱም እንዲሄድ አላሰናበተውም፤ 3 ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው ከእርሱ ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን ገባ፤ 4 የለበሰውንም ካባ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም የጦር ልብሱን፥ ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ጭምር ሰጠው። 5 ሳኦል በትእዛዝ በሚያዘምትበት ቦታ ሁሉ የዳዊት ተልእኮ የተሳካ ሆነ፤ ስለዚህም ሳኦል በጦር ሠራዊቱ ውስጥ የመኰንንነት ማዕርግ እንዲኖረው አደረገ፤ ይህም የሳኦልን የጦር መኰንኖችና ወታደሮችን ሁሉ አስደሰተ። ሳኦል በዳዊት ላይ ምቀኝነትና ቅንአት እንዳደረበት 6 ዳዊት ጎልያድን ገድሎ ሲመለስና ወታደሮችም ወደየቤታቸው በማምራት ላይ ሳሉ፥ በእስራኤል በሚገኙት ከተሞች ሁሉ የሚኖሩ ሴቶች ሳኦልን ለመቀበል ወጡ፤ እነርሱም በእልልታ እየዘፈኑና እየጨፈሩ፥ የመስንቆ ድምፅ እያሰሙ አታሞ ይመቱ ነበር። 7 ሴቶቹም ባደረጉት የአቀባበል ሥርዓት ላይ “ሳኦል ሺህ ገዳይ! ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ ገዳይ!” እያሉ ዘፈኑ። 8 ሳኦል ይህ አባባል ደስ ስላላሰኘው በጣም ተቈጥቶ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ፥ ለእኔ ግን አንድ ሺህ ብቻ ሰጡ፤ እንግዲህ ከመንገሥ በቀር ምን ቀረው!” አለ። 9 ከዚህም የተነሣ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ ቅናትና ጥርጣሬ አደረበት። 10 በማግስቱም በድንገት ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቈራኘው፤ በቤቱም ውስጥ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ በነበረው ዐይነት ለሳኦል በገና ይደረድርለት ነበር፤ ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። 11 “መትቼ ከግድግዳ ጋር አጣብቀዋለሁ!” ብሎ በልቡ አሰበ፤ ከዚህም በኋላ ጦሩን በዳዊት ላይ ሁለት ጊዜ ወረወረ፤ ዳዊት ግን ሁለቴም ዞር እያለ አመለጠ። 12 እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር ስለ ነበረ ሳኦል ዳዊትን ፈራው፤ 13 ከዚህም የተነሣ ሳኦል ዳዊትን ከፊቱ ለማራቅ የሺህ ወታደሮች አዛዥ አድርጎ ላከው፤ ዳዊትም ወታደሮቹን ወደ ጦርነት መራ። 14 እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ሆነ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። 15 ሳኦልም የዳዊትን ተልእኮ መሳካት እየተመለከተ በይበልጥ ይፈራው ጀመር፤ 16 ነገር ግን ተልእኮው የሚሳካለት መሪ በመሆኑ በእስራኤልም ሆነ በይሁዳ የሚገኝ ሕዝብ ሁሉ ዳዊትን ይወድ ነበር፤ ዳዊት የሳኦልን ልጅ ማግባቱ 17 ከዚህ በኋላ ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “የእግዚአብሔርን ጦርነት በጀግንነት ብትዋጋ ታላቅዋን ልጄን ሜራብን እድርልሃለሁ፤” ሳኦል ይህን ያለበት ምክንያት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲሞት እንጂ እርሱ ዳዊትን ለመግደል ስላልፈለገ ነው። 18 ዳዊትም “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤስ በእስራኤል መካከል እምን ቊጥር ይገባል?” ሲል መለሰለት። 19 ነገር ግን ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ከመሖላ ለመጣውና ዓድሪኤል ተብሎ ለሚጠራ ለአንድ ሌላ ሰው ተዳረች። 20 ይሁን እንጂ ሜልኮል ተብላ የምትጠራው የሳኦል ልጅ ዳዊትን ወደደች፤ ሳኦልም ይህን በሰማ ጊዜ ደስ አለው፤ 21 በልቡም “ሜልኮልን ለዳዊት እሰጣለሁ፤ እርስዋም ዳዊትን እንድታጠምድልኝ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በፍልስጥኤማውያን እጅ ይገደላል” ሲል አሰበ። ስለዚህም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን ጠርቶ “አሁን የእኔ ዐማች ትሆናለህ” አለው። 22 ባለሟሎቹንም ጠርቶ “ንጉሡ በአንተ ተደስቶአል፤ የእርሱ ባለሟሎች የሆኑት ባለሥልጣኖቹም ይወዱሃል፤ ስለዚህ የእርሱን ልጅ ታገባ ዘንድ አሁን ጥሩ ጊዜ ገጥሞሃል” ብለው ለዳዊት በግል እንዲነግሩት አዘዘ። 23 ስለዚህ የሳኦል ባለሟሎች ይህን ጉዳይ ለዳዊት በምሥጢር ነገሩት፤ እርሱም፦ “እንደእኔ ላለ ዝቅተኛ ድኻ ሰው የንጉሥ ዐማች መሆን ቀላል ይመስላችኋልን?” አላቸው። 24 ባለሟሎቹም ከዳዊት ያገኙትን መልስ ለሳኦል ነገሩት፤ 25 ሳኦልም እንደ ገና “ንጉሡ ስለ ልጁ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል አንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ገድለህ ሸለፈታቸውን እንድታመጣለት ብቻ ነው” ብላችሁ ንገሩት ሲል ባለሟሎቹን አዘዘ። ሳኦል ይህን ያደረገበት ምክንያት ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲገደልለት በማቀድ ነበር። 26 የሳኦል ባለሟሎችም ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም የንጉሡ ዐማች እንዲሆን በመታሰቡ ደስ አለው። የሠርጉም ቀን ከመድረሱ በፊት፥ 27 ዳዊትና ወታደሮቹ ዘምተው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ዳዊትም የንጉሥ ዐማች መሆን ይችል ዘንድ ሸለፈታቸውን ወደ ንጉሡ በመውሰድ ቈጥሮ አስረከበ። ስለዚህም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። 28 ሳኦል እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር መሆኑንና ልጁም ሜልኮል እርሱን እንደ ወደደችው አረጋገጠ። 29 ስለዚህም ሳኦል ዳዊትን ይበልጥ ከመፍራቱ የተነሣ በኖረበት ዘመን ሁሉ የዳዊት ጠላት ሆነ። 30 የፍልስጥኤማውያን ወታደሮች በየጊዜው እየመጡ ጦርነት ያደርጉ ነበር፤ ይሁን እንጂ በማናቸውም ጦርነት ሁሉ ከሳኦል የጦር መኰንኖች ይበልጥ ድል የሚሳካለት ለዳዊት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ዳዊት እጅግ ዝነኛ ሆነ። |