Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ጴጥሮስ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በቅድስና መኖር

1 ክርስቶስ በሥጋው መከራ የተቀበለ ስለ ሆነ እናንተም የጦር መሣሪያን እንደ ታጠቀ ሰው በዚህ ሐሳብ በርትታችሁ ተዘጋጁ፤ በሥጋው መከራን የተቀበለ ሰው ኃጢአት መሥራትን አቋርጧል።

2 ከእንግዲህ ወዲህም በቀሪው ምድራዊ ኑሮው የሚኖረው የሥጋን ክፉ ምኞት በማድረግ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም ነው።

3 አሕዛብ እንደሚያደርጉት በስድነት፥ በፍትወት፥ በስካር፥ ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ፥ ያለ ልክ ጠጥቶ በመጨፈርና አጸያፊ በሆነ የጣዖት አምልኮ ያሳለፋችሁት ዘመን ይበቃል።

4 አሁን ግን በዚህ ነገር አለመጠን ከእነርሱ ጋር በመቅበጥ ባለመሳተፋችሁ ይደነቃሉ፤ ይሰድቡአችኋልም።

5 ነገር ግን በሕይወት ባሉትና በሞቱት ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው ለእርሱ መልስ ይሰጡበታል።

6 ለሙታን ሳይቀር ወንጌል የተሰበከውም በዚህ ምክንያት ነው፤ በዚህ ዐይነት በሥጋቸው እንደ ሰው ሁሉ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈሳቸው ግን እግዚአብሔር በሚኖረው ዐይነት በሕይወት ይኖራሉ።


የእግዚአብሔር ስጦታዎችን በመልካም ማስተዳደር

7 እንግዲህ የሁሉ ነገር መጨረሻ ቀርቦአል፤ በትጋት መጸለይ እንድትችሉ የረጋ አእምሮ ይኑራችሁ፤ በመጠንም ኑሩ።

8 ፍቅር ብዙ ኃጢአትን ስለሚሸፍን ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።

9 ያለ ማጒረምረም እርስ በርሳችሁ በእንግድነት ተቀባበሉ።

10 የተለያዩትን የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታዎች በታማኝነት በማስተዳደር ከእናንተ እያንዳንዱ በተሰጠው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል።

11 የሚያስተምር፥ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚያስተምር ያስተምር፤ የሚያገለግልም እግዚአብሔር በሚሰጠው ኀይል ያገልግል፤ በዚህም ዐይነት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሁሉ ነገር ይመሰገናል፤ ክብርና ሥልጣን ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።


በመከራ ጊዜ መጽናት

12 ወዳጆች ሆይ! እንደ እሳት በሚፈትን መከራ ውስጥ ስትገኙ ያልተለመደ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ አድርጋችሁ አትደነቁ፤

13 ይልቅስ የክርስቶስ ክብር በሚገለጥበት ጊዜ እጅግ ደስ እንዲላችሁ የእርሱ መከራ ተካፋዮች በሆናችሁበት መጠን ደስ ይበላችሁ።

14 ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ የክብር መንፈስ ማለት የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ደስ ይበላችሁ።

15 ከእናንተ ማንም መከራ ሲቀበል እንደ ነፍሰ ገዳይ፥ እንደ ሌባ፥ እንደ ወንጀለኛ፥ በሰው ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ አይሁን።

16 ክርስቲያን በመሆኑ መከራ የሚደርስበት ቢኖር ግን ስለ ክርስቶስ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።

17 ፍርድ የሚጀመርበት ጊዜ ቀርቦአል፤ ፍርዱ የሚጀመረውም በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ ነው፤ ታዲያ፥ ፍርድ የሚጀመረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን?

18 ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው፦ “ጻድቅ እንኳ መዳን የሚችለው በጭንቅ ከሆነ እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች እንዴት ሊሆኑ ነው?”

19 ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሰዎች ሁለንተናቸውን ለታማኙ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ነገርን ከማድረግ አይቈጠቡ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች