Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ጴጥሮስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሕያው ድንጋይና ቅዱስ ሕዝብ

1 እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፥ ማታለልን ሁሉ፥ ግብዝነትን፥ ቅናትን፥ ማንኛውንም ዐይነት ሐሜት አስወግዱ፤

2 አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ወተት እንደሚመኙ እናንተም ለመዳን እያደጋችሁ የምትሄዱበትን ንጹሑን መንፈሳዊ ትምህርት ተመኙ።

3 ልትመኙ የምትችሉትም “ጌታ ለጋስ መሆኑን ዐውቃችሁ እንደ ሆነ ነው።”

4 ስለዚህ ሕያው ድንጋይ ወደ ሆነው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቅረቡ፤ ይህ ድንጋይ ሰዎች ንቀው የተዉት፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የተመረጠና ክቡር ዋጋ ያለው ነው።

5 ወደ ጌታ ኢየሱስ የምትቀርቡትም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ሆናችሁ ለመታነጽ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ቅዱሳን ካህናት ትሆናላችሁ።

6 በቅዱስ መጽሐፍ “እነሆ! የተመረጠና ክቡር የሆነ የማእዘን ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም” የሚል ቃል ተጽፎ ይገኛል።

7 እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን “ግንበኞች ንቀው የጣሉት ድንጋይ የማእዘን ራስ ሆነ።”

8 ደግሞም፥ “እነሆ! ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ፤ እነሆ! ሰዎችን አደናቅፎ የሚጥል አለት” ይላል። እነርሱ ቃሉን ባለማመናቸው ይሰናከላሉ፤ አስቀድመውም ለዚህ የተመደቡ ናቸው።

9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችኹ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ።

10 እናንተ ቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረት አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።


የእግዚአብሔር አገልጋዮች

11 ወዳጆች ሆይ፥ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች ስለ ሆናችሁ ከነፍስ ጋር ከሚዋጉት ከሥጋ ፍትወቶች እንድትርቁ ዐደራ እላችኋለሁ።

12 ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር እኛን ለመጐብኘት በሚመጣበት ቀን አሕዛብ መልካም ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ በእነርሱ መካከል ስትኖሩ መልካም ጠባይ ይኑራችሁ።

13 ስለ ጌታ ኢየሱስ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች ታዘዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሠ ነገሥቱም ታዘዙ።

14 ለአገረ ገዢዎችም ታዘዙ፤ እነርሱ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፥ መልካም አድራጊዎችን ለማመስገን ከንጉሠ ነገሥቱ የሚላኩ ናቸው።

15 መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

16 እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።

17 ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።


የክርስቶስ መከራ ምሳሌነት

18 እናንተ አገልጋዮች ለጌቶቻችሁ በአክብሮት ታዘዙ፤ የምትታዘዙትም ለደጎቹና ለገሮቹ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም ነው።

19 ሰው የሚመሰገነው በግፍ መከራ ሲቀበል ስለ እግዚአብሔር ብሎ ቢታገሥ ነው።

20 ክፉ አድርጋችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራ ስትቀበሉ ብትታገሡ ከእግዚአብሔር ምስጋና ታገኛላችሁ።

21 የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ክርስቶስ ለእናንተ መከራን በመቀበል ምሳሌ ሆኖላችኋል።

22 እርሱ ምንም ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉ ተንኰል አልተገኘበትም።

23 ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራን ሲቀበል በጽድቅ ለሚፈርደው አምላክ ራሱን ዐደራ ሰጠ እንጂ አልዛተም።

24 ከኃጢአት ተለይተን በጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል።

25 እናንተ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች