Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ዮሐንስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔር ልጆች

1 የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ! በእርግጥም የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ዓለም እግዚአብሔርን ስላላወቀ እኛንም አያውቀንም።

2 ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደፊት ምን እንደምንሆንም ገና አልታወቀም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እውነተኛ መልኩን ስለምናይ እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን።

3 ይህ እንደሚሆን በክርስቶስ ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ ክርስቶስ ንጹሕ እንደ ሆነ እርሱም ራሱን ንጹሕ ያደርጋል።

4 ኃጢአት ማለት የእግዚአብሔርን ሕግ ማፍረስ ስለ ሆነ ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ያፈርሳል።

5 ክርስቶስ የሰዎችን ኃጢአት ለመደምሰስ እንደ ተገለጠና እርሱም ኃጢአት እንደሌለበት ታውቃላችሁ።

6 ስለዚህ በክርስቶስ የሚኖር ሰው ሁሉ ኃጢአት አይሠራም። ኃጢአት የሚሠራም ሰው ክርስቶስን አላየውም ወይም አላወቀውም።

7 ልጆች ሆይ! ማንም አያታላችሁ፤ ክርስቶስ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ጻድቅ ነው።

8 ዲያብሎስ ከመጀመሪያው አንሥቶ ኃጢአት ስለሚሠራ ኃጢአትን የሚሠራ ሁሉ የዲያብሎስ ወገን ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ነው።

9 የእግዚአብሔር ባሕርይ በውስጡ ስለሚኖርና ከእግዚአብሔርም ስለ ተወለደ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ኃጢአት አይሠራም፤ ሊሠራም አይችልም።

10 የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፦ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም።


እርስ በርስ ስለ መፋቀር

11 ከመጀመሪያው የሰማችሁት መልእክት “እርስ በርሳችን እንፋቀር” የሚል ነው።

12 የሰይጣን ወገን እንደ ነበረውና ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየል መሆን አይገባንም፤ እርሱ ወንድሙን ስለምን ገደለው? የእርሱ ሥራ ክፉ ስለ ነበረና የወንድሙ ሥራ ግን ትክክል ስለ ነበረ ነው።

13 ወንድሞች ሆይ! ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ።

14 እኛ ወንድሞቻችንን ስለምንወድ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራችንን እናውቃለን። ፍቅር የሌለው ሰው በሞት ጥላ ውስጥ ይኖራል።

15 ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘለዓለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።

16 ፍቅር ምን እንደ ሆነ የምናውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ ስለ ሰጠን ነው፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን መስጠት ይገባናል።

17 ሰው በዚህ ዓለም ሀብት እያለው ችግረኛውን አይቶ ባይራራለት “እግዚአብሔርን እወዳለሁ” ማለት እንዴት ይችላል?

18 ልጆች ሆይ! ፍቅራችን እውነተኛና በሥራ የሚገለጥ ይሁን እንጂ በቃል ወይም በንግግር ብቻ አይሁን።


በእግዚአብሔር ፊት ያለን መተማመን

19 በዚህም እውነተኞች መሆናችንንና ወደ እግዚአብሔር ፊት ያለ ስጋት በመተማመን ለመቅረብ የምንችል መሆናችንን እናውቃለን።

20 በዚህ በኩል ልባችን ቢወቅሰንም እግዚአብሔር ከልባችን በላይ ነው፤ እርሱም ሁሉን ነገር ያውቃል።

21 ወዳጆች ሆይ፥ ልባችን የማይወቅሰን ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ሙሉ መተማመን ይኖረናል።

22 የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምንፈጽምና እርሱን ደስ የሚያሰኘውንም የምናደርግ ስለ ሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን።

23 የእግዚአብሔር ትእዛዝ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና ክርስቶስ ባዘዘንም መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።

24 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚፈጽሙ ሁሉ በእግዚአብሔር ይኖራሉ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ይኖራል። እግዚአብሔር በእኛ መኖሩን የምናውቀው እርሱ በሰጠን መንፈስ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች