ሶፎንያስ 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ፍርድ በኢየሩሳሌም ጠላቶች ላይ 1 እናንተ የማታፍሩ ሕዝብ ሆይ፥ በአንድነት ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም፤ 2 ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የጌታም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፥ የጌታም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ 3 እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ፥ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ ጌታን ፈልጉ፤ ጽድቅን ፈልጉ፥ ትሕትናን ፈልጉ፤ ምናልባት በጌታ ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። 4 ጋዛ ሰው የማይኖርባት ትሆናለች፥ አስቀሎናም ትፈራርሳለች፤ አሽዶድ በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዷታል፥ ዔቅሮንም ትነቀላለች። 5 እናንተ በባሕር ዳር የምትኖሩ፥ የከሪታውያን ሕዝብ ወዮላችሁ! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የጌታ ቃል በእናንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብሽ እንዳይኖር አድርጌ አጠፋሻለሁ። 6 የባሕሩም ዳር የግጦሽ መሬት፥ የእረኞች መስክና የበጎች በረት ይሆናል። 7 የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ፤ ጌታ አምላካቸው ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳል። 8 የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ፤ በሕዝቤም ላይ አላግጠዋል፥ በድንበራቸውም ላይ ኮርተዋል። 9 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ ይሆናሉ፥ አረም እንደ ዋጠው ስፍራና እንደ ጨው ጉድጓድ ለዘለዓለምም ይጠፋሉ፤ የሕዝቤም ትሩፍ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል። 10 ከትዕቢታቸው የተነሣ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ በሠራዊት ጌታ ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ በኩራትም ተናግረዋልና። 11 ጌታ በእነርሱ ዘንድ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርን አማልክት ሁሉ ያጠፋቸዋልና፤ የሕዝቦችም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች፥ ሁሉም በያሉበት ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ። 12 እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ። 13 እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፥ ነነዌንም ያፈራርሳታል፥ እንደ ምድረ በዳም ደረቅ ያደርጋታል። 14 መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጧ ይኖራሉ፥ ጉጉትና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፥ ድምፅም በመስኮት ይጮኻል፥ በመድረኩ ላይ ጥፋት ይደርሳል የዝግባ እንጨት ሥራ ይገለጣልና። 15 ስጋት ሳይኖርባት የተቀመጠች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፥ በልብዋም፦ “እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም” ያለች፥ እንዴት አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ ሆነች! በእርሷ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፏጫል። |