ዘካርያስ 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ሰባቱ ትንቢቶች፦ የይሁዳና የጽዮን መታደስ 1 የሠራዊትም ጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቁጣ ስለ እርሷ ቀንቻለሁ። 3 ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊት ጌታም ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል። 4 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፥ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል። 5 የከተማይቱም አደባባዮች በጎዳናው ላይ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ። 6 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በዚህ ወራት በዚህ በተረፈው ሕዝብ ዐይን ነገሩ ቢያስደንቅ፥ በውኑ ለእኔ ግን አስደናቂ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ። 7 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከፀምዕራብ ምድር እታደገዋለሁ፤ 8 በኢየሩሳሌም ውስጥ እንዲኖሩ አመጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በታማኝነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ። 9 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንት፥ መቅደሱ እንዲሠራ የሠራዊት ጌታ ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ፥ እጃችሁን አበርቱ። 10 ከነዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰው ደሞዝ፥ ለእንስሳ ኪራይ አልነበረም፤ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ስለ ነበር፥ በጠላቶቻቸው የተነሣ ወደዚያ ለሚገቡትና ለሚወጡት ሰላም አልነበራቸውም። 11 አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ በቀረው ሕዝብ ላይ አላደርግም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 12 ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፥ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠልአቸውን ይሰጣሉ፤ ለዚህም ቀሪ ሕዝብ ይህን ነገር ርስት አድርጌ እሰጣለሁ። 13 የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ በረከት መሆን እንድትችሉ አድናችኋለሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። 14 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብኩ፥ እንዳልተጸጸትኩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ 15 እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አትፍሩ! 16 እንግዲህ የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፦ እርስ በእርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ፤ በአደባባያችሁም መግቢያዎች ሐቀኛና ትክክለኛ ፍርድ ፍረዱ። 17 አንዱ በሌላው ላይ ክፉን ነገር በልቡ አያስብ፤ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፤ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል የጌታ ቃል። ሦስቱ ትንቢቶች፦ ይሁዳና አሕዛብ 18 የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 19 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም፥ የአምስተኛው፥ የሰባተኛው፥ የአሥረኛው ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ፥ የሐሤትም በዓላት ይሆናሉ፤ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ! 20 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ገና የብዙ ከተሞች ሕዝቦችና ነዋሪዎች ይመጣሉ፤ 21 በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሰዎችም፦ “ጌታን ለመለመን፥ የሠራዊት ጌታንም ለመፈለግ ኑ እንሂድ፤ እኔም እሄዳለሁ” እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። 22 ብዙ ወገኖችና ኃይለኛ አሕዛብም በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ ለመፈለግ፥ ጌታንም ለመለመን ይመጣሉ። 23 የሠራዊት ጌታም እንዲህ ይላል፦ በዚያ ዘመን ከሁሉም የአሕዛብ ቋንቋ ዐሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው፦ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና እኛም ከእናንተ ጋር እንሂድ” ይላሉ። |