Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘካርያስ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ሰባተኛ ራእይ፦ አራቱ ሰረገሎች

1 ተመልሼም ዐይኖቼን አነሣሁ፥ እነሆም፥ አራት ሰረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ።

2 በፊተኛው ሠረገላ ቀይ ፈረሶች፥ በሁለተኛውም ሠረገላ ጥቁር ፈረሶች ነበሩ፥

3 በሦስተኛውም ሠረገላ ነጭ ፈረሶች፥ በአራተኛውም ሠረገላ ዥጉርጉር ፈረሶች ነበሯቸው፤ ሁሉም ጠንካሮች ነበሩ።

4 ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረውም መልአክ መልሼ፦ “ጌታዬ ሆይ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት።

5 መልአኩም መልሶ፦ “በምድር ሁሉ ጌታ ፊት ከቆሙበት ስፍራ የሚወጡ እነዚህ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ናቸው።

6 ጥቁር ፈረሶች ያሉበት ወደ ሰሜን ይወጣል፤ ነጭ ፈረሶች ወደ ምዕራብ ይወጣሉ፥ ዥጉርጉር ፈረሶች ወደ ደቡብ ይወጣሉ” አለኝ።

7 ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፥ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቁበው ነበር፤ እርሱም፥ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ።

8 ከዚያም ጮኾ፦ “እነሆ፥ ወደ ሰሜን ምድር የሚወጡት እነርሱ መንፈሴን በሰሜን ምድር ላይ አሳርፈዋል” በማለት ተናገረኝ።


አክሊሎቹ

9 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

10 ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይ፥ ከጦብያና ከዮዳኤም ውሰድ፤ በዚያም ቀን መጥተህ ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ግባ።

11 ብርንና ወርቅን ከእነርሱ ውሰድ፥ አክሊሎችንም ሥራ፤ በሊቀ ካህኑ በኢዮሴዴቅ ልጅ በኢያሱ ራስ ላይ ድፋቸው፤ እንዲህም በለው፦

12 የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ስሙ ቁጥቋጥ የሚባል ሰው በስፍራው ይበቅላል፥ የጌታንም መቅደስ ይሠራል።

13 እርሱ የጌታን መቅደስ ይሠራል፥ ክብርንም ይጐናጸፋል፥ በዙፋኑም ላይ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል ሰላማዊ መግባባት ይኖራል።

14 ሌሎቹም አክሊሎች ለሔሌም፥ ለጦብያ፥ ለዮዳኤምና ለሶፎንያስም ልጅ ለሔን፥ በጌታ መቅደስ ውስጥ ለመታሰቢያ ይሆናሉ።

15 በሩቅ ያሉትም መጥተው የጌታን መቅደስ ይሠራሉ፤ የሠራዊት ጌታም ወደ እናንተ እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። የአምላካችሁንም የጌታን ቃል በእውነት ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች