Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘካርያስ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ስለ ሐሰት ራእይ ፍጻሜ ትንቢት

1 በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከኃጢአትና ከርኩሰት የሚያነጻ ምንጭ ይፈልቃል።

2 በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ።

3 አሁንም ቢሆን ማንም ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ፦ “አንተ በጌታ ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም” ይሉታል። ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባትና እናቱ ይወጉታል።

4 በዚያም ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው ትንቢት ስለ ራእዩ ያፍራል፥ ለማታለልም የማቅ ልብስ አይለብሱም።

5 ነገር ግን እያንዳንዱ፦ “ከታናሽነቴ ጀምሮ አገልጋይ ነበርኩ፥ መሬት አራሽ ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም” ይላል።

6 ማንም ሰው፦ “ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቁስል ምንድነው?” ብሎ ቢጠይቀው፥ እያንዳንዱም፦ “በወዳጆቼ ቤት የቈሰልኩት ቁስል ነው” ይላል።


ስለ ሰይፍ መዝሙር

7 ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ፤ በጎቹም እንዲበተኑ እረኛውን ምታ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ አዞራለሁ።

8 በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ሦስተኛው ተቈርጠው ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ፤ አንድ ሦስተኛው ክፍልም በእርሷ ይቀራል።

9 አንድ ሦስተኛውን ክፍል ወደ እሳት አስገባለሁ፤ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፤ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም፦ “ይህ ሕዝቤ ነው” እላለሁ፥ እርሱም፦ “ጌታ አምላኬ ነው” ይላል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች