ዘካርያስ 1 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለተአዝዞ የቀረበ ጥሪ 1 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፥ በስምንተኛው ወር፥ የጌታ ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 ጌታ በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር። 3 ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል ወደ እኔ ተመለሱ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ።” 4 የቀደሙት ነቢያት ለአባቶቻችሁ እንዲህ ብለው ሰብከዋል፦ “የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤’” እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፥ ይላል ጌታ። 5 አባቶቻችሁ ወዴት ናቸው? ነቢያትስ ለዘለዓለም በሕይወት መኖር የሚችሉ ይመስላችኋልን? 6 ነገር ግን ለአገልጋዮቼ ለነቢያት ያዘዝኳቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? ከዚያ እነርሱም ተጸጽተው፦ “የሠራዊት ጌታ በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ሊያደርግብን ያሰበውን እንዲሁ አድርጎብናል” በማለት ተቀበሉ። የመጀመሪያው ራእይ፦ ምድርን የሚዞሩ ፈረሶች 7 ዳርዮስ በነገሠ ሁለተኛው ዓመት፥ ሳባጥ በሚባል በዓሥራ አንደኛው ወር፥ በሀያ አራተኛው ቀን የጌታ ቃል ወደ በራክዩ ልጅ፥ ወደ አዶ ልጅ፥ ወደ ነቢዩ ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 8 እነሆ፥ አንድ ሰው በቀይ ፈረስ ላይ ተቀምጦ በሌሊት አየሁ፥ እርሱም በሸለቆው ውስጥ ባሉ በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ነበር፤ በስተ ኋላውም ቀይና ነጭ አንባላይም ፈረሶች ነበሩ። 9 እኔም፦ “ጌታዬ፥ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልኩት። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ፦ “እነዚህ ምን እንደ ሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ። 10 በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ የነበረው ሰው፦ “እነዚህ ምድርን እንዲያስሱ ጌታ የላካቸው ናቸው” ብሎ መለሰ። 11 እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ለነበረው ለጌታ መልአክ፥ “ምድርን አሰስናት፥ እነሆም፥ መላዋ ምድር በጸጥታ ዐርፋ ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት። 12 የጌታም መልአክ መልሶ፦ “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ፥ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ። 13 ጌታም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው። ንግራዊ ምላሽ 14 ስለዚህም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፥ ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ በታላቅ ቅንዓት በኢየሩሳሌምና በጽዮን ቀንቻለሁ። 15 እኔ ብዙም ሳልቆጣቸው እነርሱ ክፋትን ስላገዙት፥ በምቾት በሚኖሩት አሕዛብ ላይ እጅግ ተቈጥቻለሁ። 16 ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ፤ ቤቴ መልሶ ይገነባባታል፤ በኢየሩሳሌምም ላይ መለኪያ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ። 17 ደግሞም እንዲህም ስትል ስበክ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከተሞቼ እንደገና በብልጽግና ይሞላሉ፤ ጌታም እንደገና ጽዮንን ያጽናናል፥ ኢየሩሳሌምንም ደግሞ ምርጫው ያደርጋታል። |