ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 9 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጥበብን ለማግኘት ሰሎሞን ያቀረበው ጸሎት 1 የአባቶቻችን አምላክ፥ የምሕረት ጌታ፥ መላውን ዓለም በቃልህ ፈጠርክ፤ 2 ፍጡራንህንም ይገዛ ዘንድ፥ የሰውን ልጅ በጥበብህ ሠራህ፤ 3 ዓለምን በቅድስና ለመግዛት፥ ፍትሕንም ለመጠበቅ፥ በነፍስ ታማኝነት ያልተዛባ ፍርድ ለመስጠት፥ 4 በዙፋንህ የምትቀመጥ ጥበብን ስጠኝ፤ ከልጆችህም መሀል አትነጥለኝ። 5 እኔ አገልጋይህ የአገልጋይትህ ልጅ፥ ለአጭር ጊዜ የምኖር ደካማ ሰው፥ ስለ ሕጎችህና ስለ ፍትሕ የማላውቅ ነኝና። 6 አንድ ፍጹም ከሰዎች መካከል ቢኖር እንኳን፥ ያንተ የሆነችውን ጥበብ ካላገኘ ቁጥሩ ከከንቱዎች ነው። 7 በሕዝቦችህ ላይ እንድነግሥ መረጥኸኝ፤ በወንድና በሴት ልጆችህም ላይ እንድፈርድ ፈቀድክ። 8 በቅዱሱ ተራራ ላይ ቤተ መቅደስህን እንድገነባ፥ ድንኳንህን በተከልክበት ከተማ፥ ጥንት ያዘጋጀሃትን የቀደሰች ድንኳን ዓይነት፥ መሠዊያህን እንድሠራ አዘዝከኝ። 9 ዓለምን በፈጠርህ ጊዜ ከጐንህ ያልተለየችው፥ ሥራዎችህን የምታውቀው ጥበብ ካንተ ጋር ናት። አንተን ደስ የሚያሰኘውን፥ ከትእዛዞችህ ጋር የሚስማማውን ሁሉ ታውቃለች። 10 እኔን እንድትረዳኝ፥ ከእኔ ጋር እንድትደክም፥ አንተን የሚያስደስትህን እንድታስምረኝ፥ ከቅዱሳን ሰማያት አውጣት፤ ከከበረው ዙፋንህም ወደዚህ ላካት። 11 ሁሉንም የምታውቅና የምትረዳ በመሆኗ፥ በሥራዎቼ ላይ ሁሉ በጥንቃቄ ትመራኛለች፤ ክብሯም ትጠብቀኛለች። 12 ያኔ የማደርገው ሁሉ ተቀባይነትን ያገኛል፤ ሕዝብህን በትክክል እመራለሁ፤ ለአባቴ ዙፋንም የተገባሁ እሆናለሁ። 13 የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊያውቅ የሚችል ሰው ማን ነው? የጌታንስ ፈቃድ በውል የሚገነዘብ ማን ነው? 14 የሰዎች ግንዛቤ በስህተት የተሞላ ነው፤ አመለካከታቸውም ወላዋይ ነው፤ 15 ፈራሹ ሥጋ ነፍስን ይከብዳታል፥ ምድራዊው ድንኳንም የሚያስብ ልቡናን ይጫነዋል። 16 በምድር ላይ ያለውን ለማወቅ እንቸገራለን፤ ባጠገባችን ያለውንም ለመረዳት እንደክማለን፤ እንግዲያውስ በሰማያት ያለውን ሊያውቅ የሚችል ከቶ ማን ነው? 17 አንተ ጥበብን ባትሰጥ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ባትልክ ኖሮ፥ ማን ፈቅድህን ሊያውቅ ይችል ነበር? 18 በዚህ ዓይነት የምድር ነዋሪዎች መንገድ ተቃና፤ ሕዝቦች ደስ የሚያሰኝህን ሁሉ ተማሩ፤ በጥበብም ዳኑ። |