Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ጥበብ 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ከዓለም አንድ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ በኃይል ትዘረጋለች፤ መላውንም ዓለም ስለደኀንነቱ ስትል ታስተዳድራለች።


ሰሎሞን ለጥበብ ያለው ፍቅር

2 ከወጣትነቴ ጀምሮ ጥበብን አፈቀርሁ፥ ፈለግኋትም፤ ሙሽራዬም ላደርጋት ወሰንሁ፤ በውበቷ ተረታሁ።

3 የእግዚአብሔርን ሕይወት በመጋራት የተከበረ የትውልድ ሐረጓን ይበልጥ ከፍ ከፍ አአደረገች፤ የሁሉም ጌታ የሆነው አምላክም ይወዳታል።

4 በእርግጥ የእግዚአብሔርን እውቀት፥ ምስጢራትም ትጋራለች፤ የሚሠራውንም የምትመርጥ እርሷ ነች።

5 በዚህኛው ሕይወት ሃብትን ማግኘት ካስፈለገ፥ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ከሆነችው ጥበብ የበለጠ ሃብታም ከወዴት ይገኛል

6 የሚፈለገው በሥራ ላይ ያለው ዕውቀትም ከሆነ፥ ፍጡራኑን ሁሉ ከነደፈች ከጥበብ የተሻለ ይኖራልን

7 የምታፈቅረው ጽድቅን ከሆነ መልካም ምግባር የሥራዋ ፍሬ ነው፤ ቁጥብነትንና ጥንቁቅነትን፥ ፍትሕንና ጽናትንም የምታስተምር እርሷ ነችና።

8 ሰፊ ተሞክሮ ለማግኘት የጓጓም ካለ፥ ያለፈውን ታውቃለች፥ መጪውንም ትተነቢያለች፤ ምሳሌዎችን የምትተረጉም፥ እንቆቅልሾችን የምትፈታ ነች፤ ምልክቱንና ድንቅ ነገሮችን፥ የዓመታትና የዘመናትንም አመጣጥ ታውቃለች።

9 እኔ ሕይወቴን ትጋራ ዘንድ፥ ጥበብን ተቀበልኋት፤ በብልጽግና ጊዜ አማካሪዬ፥ በችግርና በመከራ ደግሞ አጽግኚዬ እንደምትሆን አውቃለሁና።

10 በእርሷ ምክንያት ብዙሃኑ ያደንቁኛል፤ ወጣት ብሆንም እንኳ በሽማግሌዎች ዘንድ የተከበርሁ ነኝ።

11 በምሰጠው ዳኝነት ብልኀነቴ ይታያል፤ ታላላቆችም በእኔ ይደነቃሉ፤

12 በዝምታዎቼ ወቅት ይጠባበቃሉ፤ ስናገር በጥሞና ያዳምጣሉ፤ ረዘም ላለ ጊዜ ከተናገርሁ፥ እጆቻቸውን በከንፈሮቻቸው ላይ የደርጋሉ።

13 በእርሷ አማካኝነት ሕያውነትን አገኛለሁ፤ ለተተኪዎቼም ዘላለማዊ መታሰቢያን እተዋለሁ።

14 ሕዝቦችን እገዛለሁ፤ ሀገሮችም ለእኔ ይገብራሉ፤

15 ስሜን በሰሙ ጊዜ ጨካኝ አምባገነኖች ይንቀጠቀጣሉ፤ ጀግንነቴንና ደግነቴን ለሕዝቡ አሳያለሁ።

16 ወደ ቤቴ ስመለስ የምዝናናው ከእርሷ ጋር ነው፤ እርሷ ባለችበት ምሬት የለምና። ሕየወትን ከእርሷ ጋር ሲመሩ ሥቃይ የለም፥ ተድላና ደስታ ብቻ እንጂ።


ሰሎሞን ጥበብን ለማግኘት ተዘጋጀ

17 ይህን ሁሉ አሰላስልሁ፤ ሕያውነት ከጥበብ ጋር በዝምድና መኖሯን፤

18 የከበረ ደስታ ወዳጇ፥ የማያልቅ ሃብት የሥራዋ ፍሬ መሆኑን አወቅሁ፤ ተከታዮቼን በማስተማር ማስተዋልን፥ እርሷን በማነጋገር ዝናን ማትረፍ እንደሚቻል ተገነዘብሁ፤ እናም እርሷን ፈልጌ ለማግኘት ያልረገጥሁት መንገድ የለም።

19 ደስታ ያልተለየኝ ልጅ ነበርሁ፤ ዕጣዬ ሆኖ የደረሰኝም ነፍስ ደግ ነች።

20 እንዲያውም ጥሩ በመሆኔ፥ መኖሪያዬ እንዲሆን የተሰጠኝ ሥጋ ንጹሕ ነው።

21 ነገር ግን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ጥበብን ማግኘት እንደማይቻል በመረዳቴ፥ ጥበብ የማን ስጣታ እንደ ሆነች መረዳቱ ራሱ የማስተዋል ምልክት ነው። ወደ ጌታ ጸለይሁ፥ ተማፀንሁት፥ ከልቤም እንዲህ አልሁ፦

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች