Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

መጽሐፈ ጥበብ 7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


እንደ ሌሎች ሁሉ ሰው የሆነው ሰሎሞን

1 እኔም እንደሌላው ሰው ሁሉ ሟች ነኝ፤ ከመሬት የተፈጠረው የመጀመሪያ ሰው ዘር ነኝ፤ በአንዲት እናት ማሕፀን ውስጥ ከሥጋ የተሠራሁ ነኝ፤

2 ለዓሥር ወራት ያህል ምግቤን ከደም አገኝ ነበር፤ ከወንድ ዘርና ከመኝታ ጓደኛው ካገኘው ደስታ የተገኘሁ ፍሬ ነኝ።

3 እንደተወለድሁ እኔም አየር ስቤያለሁ፥ ሁላችንን በተሸከመችውም ምድር ላይ ወድቄያለሁ፤ እንደ ሌሎች ሁሉ የመጀመሪያው ድምፄም ለቅሶ ነበር።

4 ከብዙ ጥንቃቄ ጋር በጨርቅ ተጠቅልዬ አደግሁ፤

5 የትኛውም ንጉሥ ቢሆን ከዚህ የተለየ ጅማሬ የለውም።

6 ምክንያቱም ሕይወት መግቢያዋ አንድ፥ መውጫዋም አንድ ነውና።


ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው አክብሮት

7 ስለዚህ ጸለይሁ፤ ማስተዋልም ተሰጠኝ፤ ልመናዬን አቀረብሁ፥ የጥበብ መንፈስም ወደ እኔ መጣ።

8 ከበትረ መንግሥትና ከዙፋኑም ይልቅ፥ እርሷን ከፍ አደረግሁ፤ ከጥበብ ጋር ሲነጻጸር ሀብት ምኔም አይደለም።

9 እጅግ የከበረ ድንጋይ፥ ከእርሷ አይስተካከልም፤ ወርቅም ቢሆን በእርሷ ዐይን፥ የተቆነጠረ አሸዋ አያህልም፤ ያ ከእርሷ ጋር ሲተያይ ብር፥ የጭቃ ያህል ነው።

10 ከጤናና ከውበት የበለጠ አፈቅራታለሁ፤ ከብርሃን እርሷን መረጥሁ፤ ጮራዋ ምንጊዜም አይደበዝዝምና።

11 መልካም መልካሙ ሁ፥ ከእርሷ ጋር ወደ እኔ ቀረበ፤ ከእጆችዋም ተቆጥሮ የማይዘለቅ ሃብት አገኘሁ።

12 በጥበብ ያገኘኋቸው በመሆኑም እደሰትባቸዋለሁ፤ በመጀመሪያ ላይ ግን የሁሉም እናት እርሷ መሆኗን አላወቅሁም ነበር።

13 በጥልቀት ያጠናሁትን በሰፊው አስተምራለሁ፤ የብልጽግናዋንም መጠን አልደብቅም።

14 ጥበብ የው ልጅ ሲዝቃት የማታልቅ ሃብት ነች፤ ይህንን የሚያገኙ የእግዚአብሔርንም ወዳጅነት ያገኛሉ፤ የትምህርት ጸጋ ለእነርሱ ሰጥታቸዋለችና።


መለኮታዊ አነሳሽነትን ለማግኘት ሰሎሞን ያቀረበው ልመና፥

15 የእነርሱን ፈቃድ እናገር ዘንድ ያብቃኝ፤ በተሰጠኝ ጸጋ መጠን መልካም ሐሳቦትን ላፍልቅ፤ እርሱ ወደ ጥበብ የሚመራ፥ ጥበበኞትንም የሚያሠማራ ነውና።

16 እኛ በእርሱ እጅ ነን፤ በእርግጥም እኛም አባባሎቻችንም፥ ረቂቁም ይሁን ተግባራዊው ዕውቀት ጭምር ሁሉም የእርሱ ነው።

17 ተፈጥሮን እረዳ ዘንድ፥ አስተማማኝ እውቀትን የጠኝ እርሱ ነው፤ የምድርን አቀማመጥ፥ የንጥረ ነገሮችን ጥቅም፥

18 የጊዜን መጀመሪያ፥ ማብቂያውንና አጋማሹን፥ የቀናት እርዝማኔ፥ ልውውጥና የወቅቶችን መፈራረቅ፥

19 የዓመትን ዑደትና የከዋክብት አቀማመጥ፥

20 የእንስሳትን ተፈጥሮና የአራዊትን ደመ ነፍስ፥ የመንፈሶችን ኃይልና የሰዎችን አእምሮአዊ አሠራር፥ የተክል ዓይነቶችንና የሥሮችን ፈዋሽ ባሕርይ፥ የገለጸልኝ እርሱ ነው።

21 ድብቁን ሆነ የሚታየው፤ ሁሉንም አሁን አውቄዋለሁ፤ የሁሉም ነገር ፈጣሪ የሆነች ጥበብ አስተምራኛለችና።


የጥበብ ውዳሴ

22 ጥበብ አዋቂ፥ ቅዱስ፥ የተለየ ባለ ብዙ ባሕርይ ረቂቅ፥ ተንቀሳቃሽ፥ አስተዋይ፥ እንከን የለሽ፥ ግልጽ፥ የማትደፈር፥ ቅን፥ ብልኀ፥

23 ኃያል፥ ደግ፥ የሰው ልጆች ወዳጅ፥ ቆራጥ፥ አስተማማኝ፥ የማትሸበር፥ ሁሉን የምትችል፥ ሁሉን የምትቆጣጠር፥ አስተዋይ፥ ንጹሕ፥ ረቂቅ፥ የሆኑትን መንፈሶች ዘልቆ የሚገባ መንፈሳዊ አካል አላት።

24 ጥበብ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ፈጥና መንቀሳቀስ ትችላለች፤ ንጹሕ በመሆኗም ሁሉንም ነገር ዘልቃ ትናኛለች።

25 እርሷ የእግዚአብሔር ኃይል እስትንፋስ ነች፤ የኃያሉ አምላክ ክብርም መግለጫ ነች፤ ስለዚህም ያልነጻ ነገር በውስጧ ሊገባ አይችልም።

26 የዘላለማዊ ብርሃን ነጸብራቅ፤ የእግዚአብሔር ሥራ መስተዋት፤ የደግነቱም ምስል ናትና።

27 ምንም እንኳ ብቸኛ ብትሆንም፥ ሁሉንም ማድረግ የምትችል ናት፤ ራሷ ሳትለወጥ ዓለምን ታድሳለች፤ ከትውልድ ወደ ትውልድም በተቀደሱ ነፍሶች ውስጥ በማለፍ የእግዚአብሔር ወዳጆች ነቢያትም ታደርጋቸዋለች።

28 እግዚአብሔር የሚወደው ከጥበብ ጋር የሚኖሩትን ሰዎች ብቻ ነውና።

29 ጥበብ ከፀሐይ ትደምቃለች፥ ከከዋክብት የበለጠ ታበራለች፥ ከብርሃን ጋር ስትነጻጸር፥ እርሷ ትበልጣለች።

30 ቀን በሌት ይተካል፤ ክፋት ግን ጥበብን አይረታምና።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች